የጊፋታ በዓል “ጊፋታ ለህብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሀሳብ በሶዶ ሁለገብ ስታዲየም በድምቀት ተከበረ

You are currently viewing የጊፋታ በዓል “ጊፋታ ለህብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሀሳብ በሶዶ ሁለገብ ስታዲየም በድምቀት ተከበረ
  • Post category:በዓል

AMN መስከረም 11/2018

የወላይታ የዘመን መለወጫ ”ጊፋታ”ን የመሰሉ የአደባባይ በዓላት እሴቶች ለሀገራዊ አንድነትና አብሮነት መጠናከር ያላቸውን አቅም ለመጠቀም ትኩረት መደረጉን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ገለጹ።

የጊፋታ በዓል “ጊፋታ ለህብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሀሳብ በሶዶ ሁለገብ ስታዲየም በድምቀት ተከብሯል።

ሚኒስትሯ በወቅቱም፤ በሀገሪቱ በርካታ ባህላዊና የህዝብ፣ የአደባባይ በዓላት መኖራቸውንና በዓላቱም ለህዝቦች ሰላምና አንድነት ምሰሶ ናቸው ብለዋል።

የወላይታ የዘመን መለወጫ ”ጊፋታ”ን የመሰሉ የአደባባይ በዓላት እሴቶች ለሀገራዊ አንድነትና አብሮነት መጠናከር ያላቸውን አቅም ለመጠቀም እንደሚሰራ ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

የበዓሉ እሴቶች ተጠብቀው እንዲቆዩ እንዲሁም በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገቡ እየተደረጉ ላሉ ጥረቶች ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።

ከለውጡ ማግስት ጀምሮ መንግስት ለቅርስ ጥበቃ በሰጠው ትኩረት ቅርሶች እየተጠበቁና ለቱሪስት መዳረሻነት እየዋሉ ነው ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያለው ናቸው።

እሴቶችን በዓለም አቀፍ ደረጃ በወካይነት ለማስመዝገብ በተደረገው ጥረት ባለፉት ሶስት ዓመታት ብቻ አምስት ወካይ ቅርሶችን በዩኔስኮ ማስመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም ሀገሪቱ 18 የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችን በዩኒስኮ በማስመዝገብ ከአፍሪካ ቀዳሚውን ስፍራ ይዛለች ብለዋል።

የወላይታ የዘመን መለወጫ የሆነውን ጊፋታን በዩኒስኮ ለማስመዝገብ ከዞኑና ከክልሉ እንዲሁም ከወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በጋራ በመተባበር አስፈላጊ ሰነዶች እንዲቀርቡ ተደርጎ በገምጋሚው አካል ተቀባይነት ማግኘቱን ገልጸዋል።

የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተሰማ በበኩላቸው ”ጊፋታ” ከአሮጌው ዓመት ወደ አዲሱ ዓመት የምንሸጋገርበት በዓል ነው ብለዋል።

ጊፋታ ቂምና ቁርሾን በማስወገድ በአብሮነትና በአንድነት አቅመ ደካማ ወገኖችን በመደገፍ በጋራ የሚከበር በዓል መሆኑን ገልፀው የዘንድሮው የ”ጊፋታ” በዓል የህዳሴ ግድብ ግንባታ በተጠናቀቀበት ማግስት መከበሩ ልዩ እንደሚያደርገዉ ተናግረዋል ።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review