የቦሮ ሽናሻ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ የሆነው “ጋሪ -ዎሮ” በዓል ለማህበራዊ መስተጋብር፣ ለአብሮነት መጠናከር ጉልህ ሚና የሚጫወት የሀገር ሃብት መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ነቢዩ ባዬ ገለፀዋል።
የቦሮ ሽናሻ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ በዓል የሆነው “ጋሪ-ዎሮ” በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ እየተከበረ ይገኛል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ነቢዩ ባዬ በዚህ ወቅት፤ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሃብት የታደለች፣ የአኩሪ ባህልና ታሪካዊ እሴቶች መገኛ ሀገር ናት ብለዋል።
በሀገራችን ከመስከረም ወር መጀመሪያ ጀምሮ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የተለያዩ ክብረ በዓላት እንደሚከበሩ አስታውሰው፤ በዓላቱ በህዝቦች መካከል አንድነትን፣ አብሮነትን፣ ሕብረ ብሄራዊነትን የሚያጠናክሩ ናቸው ብለዋል፡፡

ከዚህ ባለፈ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፋይዳ ያላቸው እሴቶች መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ከነዚህ በዓላት መካከል በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኘው የቦሮ ሽናሻ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ በዓል የሆነው “ጋሪ-ዎሮ” አንዱ ነው ብለዋል።
በዓሉ ረጅም ዝግጅትና ማሳረጊያ ስርዓት ያለው፣ በርከት ያለ ክዋኔዎችን በውስጡ የያዘ፣ ጥንታዊ መሰረት ያለው ውብ የኢትዮጵያ ጌጥና መልክ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
መንግስት የማህበረሰብ መገለጫ የሆኑ ባህላዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሮአዊ ሃብቶች እንዲጠበቁ፣ እንዲለሙ፣ እንዲጠኑ፣ እንዲተዋወቁና ታሪካዊ መሰረታቸውን ሳይለቁ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሻገሩ እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
የቦሮ ሽናሻ ዘመን መለወጫ የሆነው “ጋሪ-ዎሮ ” በዓል እስከ መስቀል ዋዜማ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል ።