የዘመሙ ጎጆዎችን የሚያቀኑ እድሮች

You are currently viewing የዘመሙ ጎጆዎችን የሚያቀኑ እድሮች

AMN- መስከረም 11/2018 ዓ.ም‎

‎በጭቃ እንደነገሩ በተሰራ ቤት ኑሯቸውን መግፋት ከጀመሩ ከረምረም ብለዋል፤ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ደመቀች ሁንዴ

ለዓመታት ባለመታደሱ ከእድሜ ብዛት የተነሳ በክረምት ወቅት መቃረብ በመሰለችው ‎ደሳሳ ጎጇቸው በ60ዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ ለሚገኙት ወ/ሮ ደመቀች በሰቀቀን እንዲኖሩ ግድ ብሏቸዋል።

ወይዘሮ ደመቀች ጣሪያው ዝናብን ያለከልካይ ከሚያስገባ ከስር ደግሞ ጎርፍ እንደልቡ ከሚፈስበት ቤት ውስጥ በፈተና የተሞላ ኑሮቸውን ይገፋሉ።

ወይዘሮዋ፣ በሲቃ እንባ በታጀበ ድምፃቸው እንደተናገሩት፣ በዚህች ጎጇቸው ውስጥ የዕለት ተዕለት ኑሮቸውን ለመግፋት የሰው እጅ መጠበቅ የዕለት ተዕለት ተግባራቸው እንደሆነ ይገልፃሉ።

‎ የአይን ብርሀናቸውን ማጣታቸው ከድህነት ጋር ተዳምሮ ኑሮቸውን በፈተና የተሞላ እንዲሆን አድርጎታል።

‎ ዕለት ከዕለት በሚኖሯት የሰቆቃ ህይወት ምክንያት ከመኖር መሞትን ምርጫቸው እንደሆነም ይናገራሉ።

‎ ከዚህ ቀደም የሞተን መቅበር እና ሀዘን የገጠማቸውን አባላት የማጽናናት ተልዕኮ ብቻ የነበረው መረዳጃ እድር፣ ዛሬ ላይ የሚሰጠውን አገልግሎት ከፍ በማድረግ አዛውንቶችን ወደ መጦር አድጓል።

‎ ከእነዚህ እድሮች መካከል የእነ ወ/ሮ ደመቀችን ህይወት የታደገው የሚካኤል መረዳጃ እድር ይኝበታል።

‎የዚህ መረዳጃ እድር አባል የሆኑት ወ/ሮ ደመቀች፣ የበጎ ፍቃድ ተግባር አካል የሆነው የቤት እድሳት የዘመናት እንባቸውን ያበሰላቸው በጎ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‎እድሩ የሞተን ከመቀበር ባሻገር፣ ህይወት እንዲቆይ የማድረግ ስራ ላይ አተኩሮ እየሰራ እንደሚገኝ ወይዘሮ ደመቀች ገልፀዋል።

‎እድሩ ያዘመመ ጎጃቸውን በተሻለ ሁኔታ አድሶ ያስረከባቸው መሆኑን ጠቅሰው ፣ አሁን ላይ ዝናብ እና ጎርፍ ቢመጣም ስጋት አይገባኝም በማለት ደስታቸውን ገልፀዋል።

‎ከእድሳቱ በኋላ ለመኖር ያለኝ ጉጉት ጨምሯል ያሉት ወ/ሮ ደመቀች፣ ከዚህ በኋላ ያለኝ ተስፋ ለምልሟል በማለት ደስታቸውን አካፍለዋል።

‎ቀብር ከማስፈፀም እና በሀዘን ጊዜ የእድር አባላትን ከማፅናናት ያለፈ ተግባር ሲከውኑ የዘለቁት እድሮች ፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግም ከላይ የተዘረዘሩት ሚናቸው በተጨማሪ በተለያዩ የበጎ ተግባራት ብቅ ማለት ጀምረዋል።

‎የበጎ ፍቃድ ተግባራት ላይ እየተሳተፉ፣ የነዋሪዎችን ችግር እያቃለሉ፣ የከተማዋ ልማት እና እድገት እያገዙ ይገኛሉ እድሮቹ።

‎በዚህ የእድር በጎ ፍቃድ አገልግሎት ህይወታቸው ከተቃኑ መካከል ወ/ሮ ብዙነሽ ተክለሀና ሌላኛዋ ናቸው።

‎እድሩ በወር ከ1200 ብር ከሚሰጣቸው በተጨማሪ፣ በዓላት ሲቃረቡም ለጓዳቸው የሚሆን ገንዘብ እንደሚሰጣቸው ይገልፃሉ።

‎ወርሀዊ መዋጮ የሚሸፍንላቸው እድሩ መሆኑን ወይዘሮዋ ጠቅሰው፣አመት በመጣ ቁጥር ደግሞ ብርድልብስ እደሚሰጣቸው ገልፀዋል።

‎የሚካኤል መረዳጃ እድር እንደ ብዙነሽ ላሉ እናቶች የኑሮ ውጣውረዳቸውን ለማቃለል ማህበራዊ ሀላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ ነው የእድሩ ሰብሳቢ አቶ ለማ ደሬሳ የተናገሩት።

‎የእድር አባላት ሲታመሙ የመታከሚያ ገንዘብ እንደሚያበድሩ የገለፁት ሰብሳቢው፣ ሰው ከመሞቱ በፊት በህይወት በማቆየት ላይ አተኩሮ እየሰራ እንደሚገኝ ነው የገለጹት

‎እድሩ እገዛ ለሚያስፈልጋቸው ህፃናት የአልባሳት እርዳታ ከማድረግ በተጨማሪ፣ ለአምስት አረጋውያን ቤቶችን ማደሳቸውን አስረድተዋል።

ዘመናትን ከተሻገሩ አገራዊ እሴቶች መካከል መረዳጃ እድር አንዱ ሲሆን ከቅርብ አመታት ወዲህ ደግሞ የዜጎችን ኑሮ ከማሻሻል አኳያ ሚናውን እየተወጣ ይገኛል።

‎በሔለን ተስፋዬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review