AMN – መስከረም 10/2018 ዓ/ም
የአፍሪካ ቀንድ ከ11 በመቶ የሚበልጠውን የአህጉሪቱን ህዝብ በጉያው አስጠልሏል።
በታሪክ፣ በባህል፣ በብዝሀነትና በልዩ ልዩ የተፈጥሮ ሀብቶች የዳበረው ይህ አካባቢ ካለው መጠነ ሰፊ አቅም በተቃራኒ አያሌ አመታትን በድህነትና በፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ ሆኖ አሳልፏል፡፡
በተለይ ደግሞ ላለፉት 1ዐዐ አመታት ቀጠናው ተደጋጋሚ ግጭቶችን ያስተናገደበት ወቅት እንደነበር መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡
በኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲዩት የአፍሪካ ጉዳዮች ተመራማሪ የሆኑት አቶ ሚፍታህ መሀመድ ከአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ጋር በነበራቸው ቆይታ አሁን ላይ የኢትዮጵያ ዲኘሎማሲያዊ አካሄድ ግጭትን ያስቀረና ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለውን ግንኙነት ይበልጥ ያጠናከረ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ቀጠናው ለተደጋጋሚ ግጭቶች ሳቢ የሆኑ ጉዳዮች እንዳሉትም ከነምክንያቶቻቸው ተመራማሪው ያስረዳሉ፡፡
ቀጠናው ያለበት ስትራቴጂያዊ አቀማመጥ፣ ድህነትና የተፈጥሮ አደጋዎች ለሚከሰቱ ግጭቶች ዋነኛ መንስኤ መሆናቸውንም ይጠቅሳሉ፡፡
ግጭቶች ውስጣዊ፣ ውጫዊ፣ ተፈጥሮዊ እና ሰው ሰራሽ ይዘት ያላቸው ሲሆን፤ በፖለቲካ፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በሀብት መራቆት፣ በድህነትና በመሳሰሉ ምክንያቶች አለመግባባቶች ይፈጥራል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በጅኦፖለቲካል ወሳኝ የሆነው በአፍሪካ ቀንድ የሚገኘው ቀይ-ባህርን ከሲዊዝ ካናል ጋር የሚያገናኝ አካባቢ በአለም ሀገራት ከፍተኛ ትኩረት የሚያደርጉበት አካባቢ መሆኑን የገለፁት ተመራማሪው፤ እነዚህ እና ሌሎችም ተደማምረው በአፍሪካ አለመረጋጋትና የሠላም እጦት በተደጋጋሚ ይከሰት ነበር ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የቀጠናው ሠላም እንዲጠበቅ ቁልፍ ሚናን የተጫወተች ሲሆን፤ የራስን ችግር በራስ መፍታት ከሚለው መርህ ጋር ተዳምሮ ኢትዮጵያ የቀጠናውን ሠላም ለማስጠበቅ የአንበሳውን ድርሻ ስትወጣ ቆይታለች፡፡
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ያለውን ውስብስብ የጅኦፖለቲካ ሁኔታ በፖለቲካዊ እና በዲኘሎማሲዊ መድረኮች ከተለያዩ መንግስታት ጋር በመነጋገር ከመፍታት አኳያ የራሷን ጉልህ ሚና የተጫወተች ሀገርም ናት፡፡
ከዚህ ቀደም በሰላም ማስከበር ኢትዮጵያ ትልቅ ሚና በመጫወት የሠላም አጋርነቷን ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ያረጋገጠች ብትሆንም፤ ይህ ግን ወታደራዊ መሠረት ላይ ብቻ ያተኮረ እንደነበር ገልፀዋል፡፡
ላለፉት 7 አመታት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማጠናከር፣ የኢኮኖሚ ትስስርን በመፍጠርና ሰጥቶ የመቀበል መርህን በመከተል ላይ የተመሠረተ ዲኘሎማሲ አካሄድን መከተሏ በቀጠናው ግጭት አንዳይፈጠር ጉልህ ሚና ተጫውቷል ፡፡
በቀጠናው ወደ ግጭት ገፊ ምክንያቶች ቢኖሩም ስትራቴጂያዊ ትዕግስትን የተላበሰ ዲኘሎማሲያዊ አካሄዷ ግጭትን ያስቀረና ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለውን ግንኙነት ይበልጥ ያጠናከረ መሆኑን ነው የገለፁት፡፡
ረጅም አመታትን ያስቆጠረ የሠላም ማስከበር ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ፤ ከአፍሪካ ቀንድ ባሻገር የመላው አፍሪካን አለመግባባቶች ለመፍታት አውንታዊ ሚናዋና እንደወትሮው ሁሉ ዛሬም እየተወወጣች ትገኛለች ሲሉ በኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲዩት የአፍሪካ ጉዳዮች ተመራማሪ የሆኑት አቶ ሚፍታህ መሀመድ ገልፀዋል። በበረከት ጌታቸው