ኡስማን ዴምቤሌ ወይስ ላሚን ያማል ማን የባሎን ድ ኦር አሸናፊ ይሆናል?

You are currently viewing ኡስማን ዴምቤሌ ወይስ ላሚን ያማል ማን የባሎን ድ ኦር አሸናፊ ይሆናል?

AMN-መስከረም 12/2018 ዓ.ም

ለፕሮፌሽናል እግርኳስ ተጫዋቾች በግል ከሚበረከቱ ሽልማቶች መካከል እንደ ባሎን ድ ኦር ከፍ ያለ ቦታ የሚሰጠው የለም፡፡ ከወርቃማው ኳስ ውጪ የተለየ የገንዘብ ሽልማት ባይኖረውም እውቅናው ግን የተጫዋቾችን ደረጃ በእጅጉ ከፍ ያደርጋል፡፡

ባሎን ድ ኦር ያሸነፈ ተጫዋች በክለቡ የተለየ ጉርሻ ያገኛል ፣ ስፖንሰሮች ይጎርፉለታል እንዲሁም በስፖርቱ ተከታይ ዘንድ የሚሰጠው ከበሬታ ከፍ ያለ ይሆናል፡፡ በዚህ ምክንያት ተጫዋቾች ባሎን ድ ኦርን ማሸነፍ እንደ ትልቅ ግባቸው ይይዙታል፡፡

ዛሬ ምሽት ለ69ኛ ጊዜ የሚከናወነው የዘንድሮው ባሎን ድ ኦር ለበርካቶች ክፍት ቢመስልም ኡስማን ዴምቤሌ እና ላሚን ያማል የማሸነፍ ግምት ያገኙ ተጫዋቾች ናቸው፡፡

ኡስማን ዴምቤሌ ክለቡ ፓሪሰን ዠርማ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ እንዲያሸንፍ ትልቁን ሚና ተወጥቷል፡፡ የ28 ዓመቱ ተጫዋች በቻምፒየንስ ሊጉ ስምንት ግብ አስቆጥሮ ስድስት ወደ ግብነት የተቀየሩ ኳሶችን አመቻችቶ ማቀበል ችሏል፡፡

ፓሪሰን ዠርማ የፍሬንች ሊግ ኧ እና ኩፕደ ፍራንስን እንዲያሸንፍ በዓለም የክለቦች ዋንጫ ላይ ለፍፃሜ እንዲደርስ ያገዘው ዴምቤሌ በአጠቃላይ ካደረጋቸው 53 ጨዋታዎች 35 ግቦቹን አስቆጥሮ 14 ግብ የሆኑ ኳሶችን አቀብሏል፡፡

ባርሰሎናን ለቆ ፓሪስ ከከተመ በኋላ ገና በታዳጊነቱ ሰዎች አብዝተው ስለተሰጥኦ ለምን እንዳወሩ እያሳየ የሚገኘው ኦስማን ዴምቤሌ የ2025 የባሎን ድ ኦር አሸናፊ የመሆን እድሉ ሰፊ ይመስላል፡፡

የ18 ዓመቱ ስፔናዊ ድንቅ ላሚን ያማል ታሪክ የሚሰራበት እድል አለው፡፡ በርካቶች በዚህ እድሜው ሜዳ ላይ በሚሰራው ተዓምር ባሎን ድ ኦር ይገባዋል ብለው ይሞግታሉ፡፡

ተጫዋቹ ከክለቡ ባርሰሎና እና ከሀገሩ ስፔን ጋር የተሳካ ጊዜ አሳልፏል፡፡ የላሊጋ ፣ ኮፓ ዴልሬይ እና የስፔን ሱፐር ካፕን ያሸነፈው ያማል 18 ግብ አስቆጥሮ 21 አመቻችቶ ማቀበል ችሏል፡፡ ባሎንድ ኦ ሩን ካሸነፈ ለዚህ ክብር የበቃ በእድሜ ትንሹ ተጫዋች ይሆናል፡፡

የሰፋ ግምት ካገኙት ሁለቱ ተጫዋቾች ውጪ እራሱን እና ባርሰሎናን ከፍ ያደረገው ራፊንሃ ፣ በግሉ ጥሩ የውድድር ዓመት ያሳለፈው የሪያል ማድሪዱ ኪሊያን ምባፔ ፣ ሊቨርፑልን የፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮን ያደረገው ሞሐመድ ሳላህ ፣ በተጨዋችነት ዘመኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ከባየርን ሙኒክ ጋር ዋንጫ ያሸነፈው ሀሪ ኬን እና ከፓሪሰን ዠርማ እና ከሀገሩ ፖርቹጋል ጋር ዋንጫ ያነሳው ቪቲንሃ ጭላንጭል የአሸናፊነት እድል ተሰጥቷቸዋል፡፡

አዘጋጁ ፍራንስ ፉትቦል በአጠቃላይ በ13 ዘርፎች ሽልማት ያዘጋጀ ሲሆን ስነስርዓቱም በቴአትር ዱ ሻቶሌ ይከናወናል፡፡

በሲ ቢ ኤስ ስፖርት በፕሮግራም መሪነት ዝና ያተረፈችው ኬት ስኮት እና ባሎን ድ ኦር አሸናፊ ኔዘርላንዳዊ የቀድሞ እግርኳስ ተጫዋች ሩድ ሁሌት መድረኩን ይመሩታል፡፡

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review