በሕብረ ብሔራዊ አንድነት ያጠናቀቅነው የሕዳሴ ግድባችን ለነገው ትውልድ የምናስረክበው ደማቅ አሻራችን ነው ሲሉ ከንቲባ ከድር ጁሃር ገለፁ

You are currently viewing በሕብረ ብሔራዊ አንድነት ያጠናቀቅነው የሕዳሴ ግድባችን ለነገው ትውልድ የምናስረክበው ደማቅ አሻራችን ነው ሲሉ ከንቲባ ከድር ጁሃር ገለፁ
  • Post category:ልማት

AMN – መስከረም 12/2018 ዓ.ም

በሕብረ ብሔራዊ አንድነት ለስኬት የበቃው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለነገው ትውልድ የምናስረክበው ደማቅ አሻራችን ነው ሲሉ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ተናገሩ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በስኬት መጠናቀቁን ተከትሎ በድሬዳዋ ከመስከረም 4 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው የድጋፍና የደስታ ሰልፎችና ክዋኔዎች መስከረም 12 ቀን 2018 ዓ.ም ደግሞ በአስተዳደሩ ደረጃ ተከናውኗል።

በሕዝባዊ ሰልፉ ላይ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች፣ የፀጥታና የፍትሕ አካላት፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም የሕብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል። ለበዓሉ ተሳታፊዎች የ “እንኳን ደስ አለን፤ በሕብረት ችለናል፣ ግድቡ የኔ ነው” የሚሉ መልዕክቶችን በስታዲየም ለተሰበሰበው ሕዝብ በሄሊኮፕተር በመበተን ሰልፉን አድምቀዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር፤ የሕዳሴው ግድብ ኢትዮጵያውያን በሕብረ ብሔራዊ አንድነትና ትብብር የገነባነው ደማቅ አሻራችን ነው ብለዋል። ግድቡ ለኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ መሳካት እና የሀገራችን ከፍታ ለማላቅ ወሳኝ መሆኑንም መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ኢትዮጵያውያን ከተደመርን የትኛውንም ሀገራዊ ጉዳይ ከዳር ማድረስና ከተስፋ ወደሚጨበጥ ብርሃን መሸጋገር እንደምንችል በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አሳይተናል ብለዋል።

በቀጣይም ይህንኑ ፅናትና ሕብረ ብሔራዊ አንድነታችንን በማጠናከር እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ድሬዳዋ አስተዳደር የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችን ከዳር ለማድረስ መረባረብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ለሕዳሴው ግድብ መጠናቀቅ በድሬዳዋ የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች ላደረጉት ከፍተኛ አስዋፅኦና ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review