የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ ተጠብቆ እንዲቀጥል ማህበረሰቡን አሰልጣኖ አካባቢዉን እንዲጠብቅ ማድረግ እንደሚያስፈልግ የአዲስ አበባ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ገልጿል፡፡
ቢሮዉ፣ ያሰለጠናቸውን ከአምስት ሺህ ስምንት መቶ በላይ የ1ኛ ኮርስ የአካባቢ ቅጥር ጥበቃ ባለሙያዎችን ዛሬ አስመርቋል፡፡
ሰልጣኞቹ በቀጥታ አካባቢያቸዉን ለመጠበቅ የሚሰማሩ ሲሆን፣ ቀጣዮቹን የመስቀልና የኢሬቻ በዓላትን ጨምሮ ከተማዋ ሰላምና ጸጥታ የሰፈነባት ሆና እንድትቀጥል ትልቅ ሚና ይኖራቸዋል ተብሏል፡፡
የአዲስ አበባ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ፣ የተፈጠረዉ መዋቅርና የተሰጠዉ ስልጠና ህግና ደንቦች ተከብረዉ፣ አዲስ አበባ ሰላሟ የተጠበቀ ከተማ ሆና እንድትቀጥል የሚስችላት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የቢሮ ሀላፊዋ አክለውም፣ ተመራቂ ሰልጣኞች በቁርጠኝነትና በታማኝነት ማህበረሱን እንዲያገለግሉ አሳስበዋል፡፡
የአዲስ አበባ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሚዴቅሳ ከበደ በበኩላቸዉ፣ ሰልጣኞቹ ባገኙት የንድፈ ሀሳብና የተግባር ስልጠና ማህበረሰባቸዉን በተሻለ ሁኔታ እንዲያገለግሉ ጥሪ አቅረበዋል፡፡
የአካባቢ ቅጥር ጥበቃ ባለሙያዎችም ባገኙት ስልጠና ታግዘዉ ማህበረሰባቸዉን በቅንነትና በታማኝነት ለማገለገል ዝግጁ መሆናቸዉን ለኤ ኤም ኤን ገልጸዋል፡፡
በየሺዋስ ዋለ