በመዲናዋ የመስቀል ደመራ በዓል አብሮነትን በሚያጠናክር መልኩ እንዲከበር የሃይማኖት አባቶችና የእምነቱ ተከታዮች ሚና ወሳኝ እንዳላቸዉ ተገለጸ

You are currently viewing በመዲናዋ የመስቀል ደመራ በዓል አብሮነትን በሚያጠናክር መልኩ እንዲከበር የሃይማኖት አባቶችና የእምነቱ ተከታዮች ሚና ወሳኝ እንዳላቸዉ ተገለጸ

AMN መስከረም 12/2018

በመዲናዋ የመስቀል ደመራ በዓል የህዝቦችን አብሮነት በሚያጠናክር መልኩ በድምቀት እንዲከበር የሃይማኖት አባቶችና የእምነቱ ተከታዮች ሚና ወሳኝ መሆኑን የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሊዲያ ግርማ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ፣ የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የ2018 ዓ.ም የደመራና የመስቀል በዓል አከባበርን በተመለከተ የማጠቃለያ የውይይት መድረክ እያካሄዱ ይገኛሉ።

በመድረኩ የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሊዲያ ግርማ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው እንዲሁም ከሁሉም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች፣ የስራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የቢሮው ኃላፊ ሊዲያ ግርማ የመስቀል ደመራ በዓልን ጨምሮ በመስከረም በድምቀት የሚከበሩ ሃይማኖታዊና ህዝባዊ የአደባባይ በዓላት የኢትዮጵያውያን በብዝኃነት ያሸበረቁ የአንድነት መገለጫ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የህዝቦችን ወንድማማችነትና እህትማማችነት በማጎልበት የማይተካ ሚና እንዳላቸውም አስረድተዋል። የዘንድሮው የመስቀል ደመራ በዓል ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በተመረቀበትና ታላላቅ ሜጋ ፕሮጀክቶች በተበሰሩ ማግስት የሚከበር መሆኑ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።

በዓሉ በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ዝግጅት መደረጉን ያገለጹት ኃላፊዋ፥ የሃይማኖት አባቶችና የበዓሉ ታዳሚዎችም በዓሉን ሃይማኖታዊ ትውፊቱን በጠበቀና አብሮነትን በሚያጠናክር መልኩ እንዲከበር የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ፣ የሀድያና ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የቦርድ ሰብሳቢ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ፥ መስቀል የሰላም፣ የአንድነት፣ የድኅነት በዓል ነው ብለዋል።

የመስቀል ደመራ በዓልን ለማክበር ወደ ማክበሪያ ስፍራ የሚመጡ የእምነቱ ተከታዮችም የበዓሉን ሃይማኖታዊ ትውፊትና ሥርዓት በመጠበቅ ማክበር እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

የአዲስ አበባ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ መጋቢ ታምራት አበጋዝ፥ የዓለም ቅርስ የሆነው የመስቀል ደመራ በዓል ብዝኃነትና አንድነትን በሚያንጸባረቅ መልኩ በአደባባይ የሚከበር በዓል መሆኑን መግለጻቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) 8ኛ ጉባኤውን በአዘርባጃን ባኩ በ2006 ዓ.ም ባካሄደበት ወቅት የመሰቀል ደመራ በዓልን የማይዳሰስ የዓለም ቅርስ አድርጎ መመዝገቡ ይታወሳል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review