የ2018 የመስቀል ደመራ በአል በድምቀት ለማክበር የሚያስችለው ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ-ክህነት የአስተዳደር መምሪያ ስራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ገለጹ፡፡
የቤተ ክህነቱ ስራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የበዓሉን አከባበር አስመልክተው በሰጡት መግለጫ የመስቀል ደመራ በዓል የሰላም ምልክት የአንድነትና አብሮነት እሴትን የሚያጠናክር ነው ብለዋል፡፡
የመስቀል ደመራ በዓል ከኃይማኖታዊ አስተምህሮው ባሻገር የኢትዮጵያዊያን አንድነት፣ መተባበርና አብሮነት የሚገለጽበት መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከሚከበሩ ሃይማኖታዊ የአደባባይ በዓላት አንዱ የመስቀል ደመራ በዓል መሆኑም ገልጸዋል።
ደመራ መጨመር፤ መሰብሰብ የሚል ትርጓሜ ሲኖረው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ምዕመናን ደመራ ደምረው ችቦ እያበሩ በዓሉን በሃይማኖታዊ ስርዓት እንደሚከበር መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በዓሉ የአንድነት፣ የፍቅር፣ የይቅርታ፣ የአብሮነት፣ የምስጋናና የተስፋ እሴቶች የሚገለጹበት ኃይማኖታዊ ክብረ-በዓል ሲሆን፤ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በደማቅ ሁኔታ ይከበራል ብለዋል።
በዚህም በአሉ በተሰካ ሁኔታ ማክበር የሚያስችል ኮሚቴ በማዋቀር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በመቀናጀት አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልፀዋል።
ምዕመናኑ በዓሉ በሰላም እንዲከበር የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም የቤተ ክህነቱ ስራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ጥሪ አቅርበዋል።
ምዕመናን በአሉን ሲያከብሩ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማ እና የቤተክርስቲያኒቱን አርማ ብቻ መጠቀም እንዳለባቸውም አሳስበዋል።