አለም አቀፍ ሁነቶችን በመተንበይ የሚታወቁት ባባ ቫንጋ ስለ 2026 ዓመት ምን አሉ

You are currently viewing አለም አቀፍ ሁነቶችን በመተንበይ የሚታወቁት ባባ ቫንጋ ስለ 2026 ዓመት ምን አሉ

AMN – መስከረም 12/2018 ዓ.ም

ቡልጋሪያዊቷ ባባ ቫንጋ ባለፉት አመታት የተለያዩ አለም አቀፍ ሁነቶችን በመተንበይ ከፍተኛ እውቅናን አግኘተዋል።

ከ28 አመት በፊት ህይወታቸው ያለፈው ባባ ቫንጋ እስከ 2030 ድረስ አለማችን የምታስተናግዳቸውን አበይት ክስተቶች ተንብየዋል፡፡ በ12 አመታቸው የአይን ብርሃናቸውን ካጡ በኋላ የወደፊቱን የመተንበይ ብቃት እንዳዳበሩ የሚነገርላቸው ባባ ቫንጋ፤ የመስከረም 11ዱን የኒውዮርክ መንትያ ህንጻዎች ጥቃት፣ የጃፓን ፉኪሺያማ ኑክሌር ማብላያ መፈንዳት ፣ የሶቪየት ህብረት መፈራረስ እና ካንሰር የተባለ በሽታ ቀጣይ ስጋትነትን አስቀድመው ተንብየዋል።

የዘንድሮውን የፈረንጆቹ አመት ጨምሮ በባለፈው እና ከዛ በፊት በነበሩ ቅርብ አመታት ያስቀመጧቸው አንዳንድ ትንበያዎችም እውነት ሆነው ታይተዋል። በ2024 በማይናማር የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ፣ የበሽር አላስድ መንግስት ውድቀት፣ የዩክሬን እና ሩስያ ጦርነት የባባን የትንበያ አቅም ያሳዩ የቅርብ ጊዜ ተጠቃሽ አለም አቀፍ ሁነቶች ናቸው።

በዚህ አመት 3ተኛው የአለም ጦርነትን ጨምሮ ፣ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ተጽዕኖ በከፍተኛ ሁኔታ ማደግ ፣ የኤሊያኖች ወደ ምድር መምጣት ፣ ተፈጥሯዊ አደጋዎች መበርከት እና ሌሎችም አበይት ሁነቶች እንደሚኖሩ ተንብየዋል፡

👉 የ3ኛው የአለም ጦርነት

ባባ በ2026 የአለምን ቅርጽ የሚቀይሩ ሁነቶች እንደሚከሰቱ ካስቀመጧቸው አበይት ሁነቶች መካከል የ3ተኛው የአለም ጦርነት መከሰት የበርካቶችን ቀልብ ይዟል። ወቅቱ አለም ከመቸውም ጊዜ በበለጠ በከፍተኛ ጂኦፖለቲካዊ ውጥረት ውስጥ የምትገኘበት ጊዜ እንደሆነ የተለያዩ አለም አቀፍ ተንታኞች ይናገራሉ።

እስራኤል ከተለያዩ የአካባቢው ሀገራት ጋር ፍጥጫ ውስጥ ትገኛለች ፣ ቻይና ታይዋንን ለመጠቅለል ጦርነት ልትከፍት እንደምትችል ስጋት አለ ፣ ዩክሬን እና የሩስያ ጦርነት አሁንም እንደቀጠለ ነው። በትንበያው መሰረትም ከምስራቅ አውሮፓ የሚቀሰቀሰው ጦርነት ወደ ምዕራቡ አለም ተስፋፍቶ ከባድ ውድመትን ሊያስከትል ይችላል። በጋዛ እየተካሄደ የሚገኘው ጦርነት ወደ ሌሎች አካባቢዎችም እንደሚዛመት ተነግሯል፤ እነዚህ ግጭቶች የሚፈጥሩት ግንኙነት የ3ኛው የአለም ጦርነትን ሊያስከትል ይችላል ነው የተባለው።

👉 የኤሊያኖች ወደ ምድር መምጣት

ባባ ቫንጋ በ2026 ከሚፈጠሩ አብይት ክስተቶች መካከል ኤሊያን የሚባሉ እንግዳ ፍጥረታት ወደ ምድር መምጣትን አስቀምጠዋል። በትንበያው መሰረትም በሚቀጥለው አመት በሚካሄድ አለም አቀፍ የስፖርት ውድድር ላይ ግዙፍ የኤሊያኖች መንኮራኩር ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ ራሱን እንደሚገልጥ ተንብየዋል። በ2026 የክረምት ኦሎምፒክ ፣ በአሜሪካ ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ አዘጋጅነት የሚደረገው የአለም ዋንጫ ዋና ዋና ስፖርታዊ ሁነቶች ናቸው።

👉 የአየር ንብረት ለውጥ እና የሰው ሰራሽ አስተውሎት ተጽዕኖ ማደግ

በዚሁ አመት ከ7-8 በመቶ የምድርን ቅርጽ የሚለውጡ እሳተ ጎመራዎች ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ እና ሌሎችም ተፈጥሯዊ አደጋዎች እንደሚከስቱ ተነግሯል። ሰው ሰራሽ አስተውሎቶች (ኤ.አይ) በሰዎች ግንኙነት ውስጥ ፣ ስራዎችን በመንጠቅ እና በሌሎች ማህበራዊ መስተጋብሮች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ ተንብየዋል።

በፈረንጆቹ 1911 በቡልጋሪያ የተወለዱት ባባ ቫንጋ በ85 ዓመታቸው ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን፤ እስከ 2030 ዓመት ድረስ ሊከሰቱ የሚችሉ የዓለማንን አበይት ክስተቶችን ዘርዝረዋል፤ በፈረንጆቹ 5079 ላይ የዓለም ፍጻሜ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።

በዳዊት በሪሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review