ቢሮው ከፍተኛ የገንዘብ መጠን የመንግስትን ጥቅም ለማሳጣት የሚያስችል ግድፈት ፈፅመው የተገኙ 10 የሂሳብ ባለሙያዎችና ኦዲተሮች የሙያ ፈቃድ እንዲሰረዝ ጥያቄ ማቅረቡን ገለፀ

You are currently viewing ቢሮው ከፍተኛ የገንዘብ መጠን የመንግስትን ጥቅም ለማሳጣት የሚያስችል ግድፈት ፈፅመው የተገኙ 10 የሂሳብ ባለሙያዎችና ኦዲተሮች የሙያ ፈቃድ እንዲሰረዝ ጥያቄ ማቅረቡን ገለፀ

AMN – መስከረም 12/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ የ2017 በጀት ዓመት የ13 ግብር ከፋዮች መዝገብ በማዘጋጀት ካቀረቡ ባለሙያዎች መካከል ከፍተኛ የገንዘብ መጠን የመንግስትን ጥቅም ለማሳጣት የሚያስችል ግድፈት ፈፅመው የተገኙ 10 የሂሳብ ባለሙያዎችና ኦዲተሮች የሙያ ፈቃድ እንዲሰረዝ ጥያቄ ማቅረቡን ገልጿል፡፡

ቢሮው ይኸን ጥያቄውን ያቀረበው በታክስ አስተደደር አዋጅ 983/2008 አንቀፅ 48 ንዑስ አንቀፅ 2(ሀ) መሰረት ለኢትዮጲያ የሂሳብና ኦዲት ቦርድ መሆኑንም ቢሮው ለኤ ኤም ኤን በላከው መረጃ ገልጿል፡፡

በቢሮው የሙያ ፈቃዳቸው እንዲሰረዝ ጥያቄ የቀረበባቸው 10 የሂሳብ ባለሙያዎችና ኦዲተሮች በቦርዱ የሙያ ፈቃድ የተሰጣቸው መሆናቸውንም አሳውቋል፡፡

ከዚህም ባሻገር ቢሮው ከሂሳብ ባለሙያዎችና ኦዲተሮች የሂሳብ መዝገብ አዘገጃጀት ላይ በሚስተዋሉ ግድፈቶች ላይ ከቦርዱና ከሙያ ማህበራት ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶች ማካሄዱና የሂሳብ ባለሙያዎችና ኦዲተሮች ለቢሮው የሚያዘጋጁት የሂሳብ መዝገብ ማሟላት የሚገባቸው ጉዳዮች በተመለከተ በመፅሔት በማዘጋጀት ለሁሉም አካል እንዲሰራጭ ማድረጉም ተጠቁሟል፡፡

ቢሮው የሙያ ፈቃዳቻው እንዲሰረዝ ጥያቄ ያቀረበባቸው የሂሳብ ባለሙያዎችና ኦዲተሮች በ2017 በጀት ዓመት ለግብር ከፋዮች ሂሳብ መዝገብ አዘጋጅተው በቅድመ ኦዲት ከፍተኛ ግድፈት የተገኘባቸውና በታክስ ስወራ የመንግስትን ጥቅም ሊያሳጡ የነበሩ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ግብር ከፋዮች ቢሮው የሙያ ፈቃድ ስረዛ በተጠየቀባቸው የሂሳብ ባለሙያዎችና ኦዲተሮች ተዘጋጅተው የሚቀርቡ የሂሳብ መዝገቦችን የማይቀበል መሆኑን በመረዳት የስም ዝርዝራቸውን ከቦርዱ በመጠየቅ የሙያ ስነ ምግባሩን ጠብቀው በሚሰሩ የሂሳብ ባለሙያዎችና ኦዲተሮች የሂሳብ መዝገቡን በማሰራት እንዲያቀርብ ማሳሰቡን ቢሮው የላከው መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review