በአፍሪካ የከተማ እድገት እና መስፋፋት እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ በኢኮኖሚ ፍላጎት የተነሳ መኖሪያቸውን በከተማ የሚያደርጉ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ይገኛል።
በተለይም በዋና ከተማዎች የሚገኝ መጠኑ ከፍ ያለ የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ ሰዎች ወደ ከተሞች እንዲሳቡ ማድረግ ስለመቻሉ የወርልድ ፖፑሌሽን መረጃ ይጠቁማል።
በዚህ የተነሳም ከሁለት ሚሊየን በላይ ነዋሪ ያላቸው የአፍሪካ ከተሞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ይገኛል።
ባለፉት አስርት አመታት እየታየ ያለው እድገት በፈረንጆቹ 1975 ከነበረው ቁጥር ጋር ሲወዳደር ከፍተኛ ለውጥ የታየበት ነው።
በጊዜው በጣት የሚቆጠሩ የአፍሪካ ከተሞች 6 ሚሊዮን ነዋሪ በመያዝ ተጠቃሽ ሲሆኑ፣ በአሁኑ ወቅት ግን 23 ሚሊዮን ነዋሪን በመያዝ በአለም አቀፍ ደረጃ ተፎካካሪ የሆኑ ከተሞች በአህጉሯ መፈጠር ችለዋል።
ግዙፍ ከተሞች በስራ እድል ፈጠራ ፣ በመሰረተ ልማት ፣ በመኖሪያ ቤት እና በሌሎችም ከኢኮኖሚ ጋር በተገናኙ ጉዳዮች ያላቸው አቅም ከአጎራባች ትናንሽ ከተሞች እና ከገጠር አካባቢዎች ዜጎችን በመሳብ የነዋሪያቸው ቁጥር አድጓል።
ካይሮ፣ ኪንሻሳ እና ሌጎስ 17 ሚሊየን እና ከዛ በላይ ነዋሪን በመያዝ ከአፍሪካ በቀዳሚነት ከሚጠሩት ከተሞች መካከል ናቸው።
የአፍሪካ ከተሞች እድገት እና የነዋሪዎች ቁጥር መጨመር ለስነ-ህዝባዊ አሰፋፈር እና ለኢኮኖሚ እድገት ሚናው የላቀ መሆኑ ይነገራል።
በዚሁ ልክ ይህ የህዝብ ቁጥር በትክክለኛው የከተማ ፖሊሲ ካልተመራ በመሰረተልማት ፣ በትራንስፖርት ፣ በመኖሪያ ቤት እና ሀይል አቅርቦት ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖረው መረጃው ጠቁሟል።
ይህን የህዝብ ቁጥር ወደ ኢኮኖሚያዊ አቅም ለመቀየር ከተሞች በስራ እድል ፈጠራ እና በመሰረተ ልማት ላይ የሚከተሉት አካሄድ ወሳኝ መሆኑም ተነስቷል።
በ2025 በርካታ ነዋሪዎችን በመያዝ ከ23 ሚሊዮን በላይ ህዝብ የሚኖርባት የግብጽ መዲና ካይሮ ቀዳሚ ስትሆን፤ የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎዋ ኪንሻሳ 17 ሚሊየን ነዋሪን በመያዝ ትከተላለች።
ሌጎስ ፣ ሉዋንዳ እና ዳሬሰላም ከሶስት እስከ አምስት ያለውን ደረጃ ሲይዙ፤ አዲስ አበባ ከ5 ሚሊዮን 956 ሺህ በላይ ህዝብ መኖሪያ በመሆን 9ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
በዳዊት በሪሁን