ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በህብረት ከቆምን ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም ማሳካት እንደምንችል ያሳየንበት ነው ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ተናገሩ።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በስኬት መጠናቀቁን ተከትሎ በሲዳማ ክልል በሀዋሳ ከተማ ሕዝባዊ የደስታ መግለጫና የድጋፍ ሰልፍ እየተካሄደ ይገኛል።
በሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ግድቡ በህብረት ከቆምን ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ማሳካት እንደምንችል ያሳየንበት ነው ብለዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ ኢትዮጵያውያን የውሃ ሀብታችንን ለልማት ለማዋል የነበረንን የዘመናት ቁጭትና ፍላጎት እውን ያደረግንበት ነው ሲሉም መግለፃቸው ኢዜአ ዘግቧል።

አብሮነትን በማጠናከር በህብረት ስንነሳ ሌሎች ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶችን እውን ማድረግ እንደምንችል ያሳየንበት የኩራታችን ምንጭ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
የግድቡ ግንባታ በርካታ ጫናዎችንና ፈተናዎችን በማለፍ ያለማንም ድጋፍ በኢትዮጵያውያን ትብብርና መንግስት ባሳየው ቁርጠኝነት ለፍጻሜ መብቃቱን አስታውቀዋል።
የዛሬው ትውልድ በሀገር ልማት ለዘመናት የሚታወስበት ደማቅ አሻራውን ያሳረፈበት ግድብ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይ ሌሎች ትልልቅ የልማት ሥራዎችን በአንድነት ለማሳካት የህዳሴው ግድብ መሠረት መጣሉን ጠቅሰዋል።
በቀጣይም ሀገራዊ አንድነትን አጠናክሮ በማስቀጠል ትውልድ ተሻጋሪ ሌሎች ልማቶችን ለማከናወን ተግተን በህብረት ልንሰራ ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።