በሰሜን ፊሊፒንስ ካጋያን ክፍለሃገር የምትገኘውና የባቡያን ደሴቶች አንዷ የሆነችው ፓኑታን ደሴት በትናንትናው እለት ራጋሳ በተሰኘ ከባድ አውሎ ነፋስ መመታቷን ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች አካባቢውን ለቀው ወጥተዋል፡፡
በዓመቱ ከታዩ አውሎ ነፋሶች ከባዱ እንደሆነ የተገለፀው አውሎ ነፋስ መከሰቱን ተከትሎም፣ በአካባቢው ያሉ ትምህርት ቤቶች እና የመንግስት ተቋማት ተዘግተዋል፡፡
ምንም እንኳን አውሎ ነፋሱ አሁን የቀነሰ ቢመስልም፣ ለህይወት አስጊ የሆነ ጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት ሊያስከትል እንደሚችል ባለስልጣናት አስጠንቅቀዋል፡፡
እስካሁን ከአንድ ሰው እና መሰረተ ልማት ጉዳት ውጪ የደረሰ ከባድ ጉዳት አለመኖሩን የሃገሪቱ ባለስልጣናት አስታውቀዋል፡፡
በሰዓት 285 ኪሎ ሜትር እየተጓዘ ያለው አውሎ ነፋስ፣ ወደ ደቡብ ቻይና እና ታይዋን እየገሰገሰ መሆኑን መረጃያዎች ማሳየታቸውንም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
መረጃውን ተከትሎም ሆንግ ኮንግ ከአሁኑ የንግድ ተቋማትን እና ትምህርት ቤቶችን በመዝጋትና በመቶዎች የሚቆጠሩ በረራዎችን የሰረዘች ሲሆን፣ በጉዎንደንግ ግዛት ከ300 ሺህ በላይ ሰዎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ በማድረግ የቅድመ ጥንቃቄ ሥራ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
አውሎ ነፋሱ በዚህ ሳምንት በቀጣናው የጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት ስጋቶችን መቀስቀሱም ተመላክቷል፡፡
በሊያት ካሳሁን