የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ(ዶ/ር) የኢጋድ ተልዕኮ ቢሮን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኒው ዮርክ በይፋ ከፈቱ

You are currently viewing የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ(ዶ/ር) የኢጋድ ተልዕኮ ቢሮን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኒው ዮርክ በይፋ ከፈቱ
  • Post category:አፍሪካ

AMN መስከረም 13/2018

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ያለውን የባለብዙ ወገን ትብብር ለማጠናከር በቁርጠኝነት እንደሚሰራ የተቋሙ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ(ዶ/ር) ገልጸዋል።

ዋና ፀሐፊው የኢጋድ ተልዕኮ ቢሮን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኒው ዮርክ በይፋ ከፍተዋል።

የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ(ዶ/ር) ተቋሙ ህንጻ ገንብቶ ከማስመረቅ ባለፈ ለባለብዙ ወገን ትብብር ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።

በዓለም መድረክ የቀጣናው ቅድሚያ ትኩረቶች ተሰሚነት እንዲያገኙ ያለውን ጠንካራ ፍላጎት እንደሚያመላክትም ገልጸዋል።

አዲስ የተከፈተው የኢጋድ ቋሚ የተልዕኮ ቢሮ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቀጣናዊ ተቋሙ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጋር በመሆን በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አቅም ለመገንባት እና የዜጎች የዘላቂ ልማት ተጠቃሚነትን ለማሳለጥ እያከናወነ ያለውን ስራ የበለጠ እንደሚያጎለብት አመልክተዋል።

ቢሮው ኢጋድ ሰላማዊ፣ የተረጋጋ እና የበለጸገ ቀጣናን እውን የማድረግ የጋራ ጉዞ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ መክፈቱንም ነው ጨምረው የተናገሩት።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢጋድ ቋሚ መልዕክተኛ ቸርነት ሀሪፎ በቢሮው ቋሚ ታዛቢ ሆነው እንደሚያገለግሉ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ(ዶ/ር) የተመራ ልዑክ በኒው ዮርክ እየተካሄደ በሚገኘው 80ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ እየተሳተፈ ይገኛል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review