በእግርኳሱ ዓለም በግል ከሚበረከቱ ሽልማቶች ውስጥ እንደ ባሎን ድ ኦር ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው የለም፡፡ በፍራንስ ፉትቦል መፅሔት አማካኝነት እኤአ 1956 ላይ መሰጠት የጀመረው ሽልማቱ ሁሉንም ያስማማ ሆኖ አያውቅም፡፡ ሁሌም ’’እከሌ ይገባው ነበር’’ ማለት የተለመደ ነው፡፡ ትናንት ምሽት የተከናወነው 69ኛው የባሎን ድ ኦር ሽልማት በወንዶች ኡስማን ዴምቤሌ አሸንፏል፡፡ ሁሉንም ባይሆን በርካቶችን ያስማማ ምርጫ ተደርጎ ተወስዷል፡፡
ከዚህ ቀደም ግን ከፍተኛ ውዝግብ ያስነሱ አሸናፊዎች ነበሩ፡፡ ሽልማቱ ይገባናል ብለው የሚያስቡ ተጫዋቾች አሁንም ድረስ በቁጭት ይናገራሉ፡፡ ለመሆኑ የባሎን ድ ኦር አሸናፊዎች እንዴት ይለያሉ? እነማን ድምፅ ይሰጣሉ? አሁን ላይ በሁለት መንገድ ምርጫው ይከናወናል፡፡
መጀመሪያ አዘጋጁ ፍራንስ ፉትቦል ከ ሌኪፕ ጋዜጣ ጋር በመተባበር ተጫዋቾች በውድድር ዓመቱ ባሳዩት ብቃት 30 ዕጩዎችን ይፋ ያደርጋል፡፡ በዚህ ምርጫ ላይ በአንዳንድ አጋጣሚ የተወሰኑ የቀድሞ ተጫዋቾች ድምፅ እንዲሰጡ ይደረጋል፡፡ በመቀጠል በፊፋ ደረጃ እስከ 100 የተቀመጡ ሀገራት ውስጥ የሚገኙ ጋዜጠኞች ከ30 ዕጩዎች ውስጥ ከአንድ እስከ 10 እንዲመርጡ ይደረጋል፡፡
በጋዜጠኞቹ አንደኛ ደረጃ የተሰጠው 15 ነጥብ ፣ ሁለተኛ የተመረጠው 12 ነጥብ እንዲሁም ሦስተኛ ላይ የተቀመጠው ደግሞ 10 ነጥብ እያለ እስከ 10 የተመረጡ ተጫዋቾች እንደየ ደረጃቸው ነጥብ ያገኛሉ፡፡ የተሰጡት ድምፆች ተሰብስበው አሸናፊው የሚለይ ይሆናል፡፡ ምናልበት በነጥብ እኩል ከሆኑ ደጋግሞ 10 ውስጥ የገባው ተጫዋች ቅድሚያ ይሰጠዋል፡፡
ጋዜጠኞቹ ተጫዋች ሲመርጡ ሦስት ጉዳዮችን ከግምት እንዲያስገቡ ይነገራቸዋል፡፡ ተጫዋቹ በውድድር ዓመቱ ያሳየው የግል ብቃት ፣ ከቡድኑ ጋር ያገኘው ስኬት እና በሜዳ እና ከሜዳ ውጪ የተጫዋቹ ባህሪን እንዲያዩ ይመከራሉ፡፡ ከዚህ ቀደም ባሎን ድ ኦር መሰጠት ከጀመረበት 1956 እስከ 1995 ድረስ አውሮፓውያን ተጫዋቾች ብቻ ነበር በሽልማቱ ይካተቱ የነበረው፡፡
ከ1995 እስከ 2007 የተለያየ ሀገር ዜግነት ያላቸው በአውሮፓ የሚጫወቱ ሁሉም ተጫዋቹች እንዲካተቱ ተደረገ፡፡ ከ2007 እስካሁን ድረስ በየትኛውም የዓለም ክፍል ይጫወቱ እጩ ውስጥ እንዲገቡ ተደርጎ እየተሰራበት ነው፡፡ ከ2007 እስከ 2015 በነበረው ጊዜ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞች እና ተጫዋቾችም ድምፅ ይሰጡ ነበር፡፡ አሁን ግን ይህ አሰራር ቀርቷል፡፡
በሸዋንግዛው ግርማ