የመስቀል በዓል አከባበር በቱለማ እና አካባቢው

You are currently viewing የመስቀል በዓል አከባበር በቱለማ እና አካባቢው

‎AMN – መስከረም 14/2018 ዓ.ም

መስቀል በዓል ሲቃረብ ሁሉም ይሰባሰባል። የተጣላም ይታረቃል። በባህል እና ወጉ መሰረት ቂም እና ቁርሾ ለብራ ወቅት ማሸጋገር የተከለከለ ነው።

ይህ ብቻ አይደለም፤ የመስቀል በዓል እንስሳቶች ከሜዳ ያለማንም ከልካይ የሚቦሩቁበት ነው። ላሞች እንኳን በመስቀል ቀን ከነጥጃቸው ወደ መስክ የሚለቀቁበት የነፃነት ቀናቸው ነው።

‎የመስቀል ወቅት በህይወት ያሉ የቤተሰብ አባል መሰባሰባቸው የግድ ነው። ቂም እና ቁርሾ የያዙ ሰዎችም እልባት የሚያገኙት በዚሁ ቀን ነው። ለእርቅም ለምርቃትም የቤተሰብ አባላት መገኘታቸው የግድ ይላቸዋል።

‎የመስቀል በዓል አከባበር በተለያዩ አከባቢዎች እንደ ባህል እና ወጉ ይለያያል። ከሀይማኖታዊ ዳራው ባሻገር ኢትዮጵያውያን በተለያዩ አካባቢዎች በዓሉን በልዩ ልዩ ሁኔታ በደማቅ ሁኔታ ሲያከብሩ ዘመናት ተቆጥረዋል።

የመስቀል በዓል ከሚከበርባቸው መካከል በኦሮሚያ ክልል ቱለማ እና አካባቢው አንዱ ነው። በዚህ በዓል ኤ ኤም ኤን ዲጅታል ከአባ ገዳ ፍቃዱ አበራ ጋር ቆይታ አድርጓል። አባ ገዳ ፍቃዱ የበቾ አባ ገዳ ሲሆኑ የቱለማ አባ አለንጋ ናቸው። በቱለማ እና አካባቢው የመስቀል በዓል አከባበርን በተመለከተ ባህል እና ወጉን አጫውተውናል።

‎የበዓል አከባበሩ የሚጀምረው ከዋዜማው ዳመራ ወይም ችቦ በማብራት እንደሆነ አባ ገዳ ፍቃዱ ይገልፃሉ። ደመራ የማብራት ስርዓት እንደየቤተሰቡ ቅደም ተከተል ከአባት ወይም ከአባ ወራ ችቦ ለኩሶ መውጣት ይጀመራል።

‎የቤቱ አባወራ ሁለት ችቦ ለኩሶ “ብራን ኢፋ በጋ ኢፋቲን ኑባስተኤ” ወይም “እንኳን ወደ ብርሀን ተሸጋገርን” እያሉ እየመረቁ ወደ ደጃፍ ይወጣሉ፡፡

‎ቀጥሎም ሁሉም ቤተሰብ ደመራ የማብራት ስርዓት ካከናወነ በኋላ፤ በአንድ ገበታ ቀርበው ማዕድ ይቋደሳሉ። ይህ ከተጠናቀቀ በኋላ ወጣት ወንዶች ”ኦፈልቲ” ወይም ምርቃት ተቀብለው ባህላዊ ጭፈራ እንደሚጫወቱ ይገልፃሉ።

‎በመስቀል በዓል አከባበር ስርዓቱ ለእንስሳቶቹም የችቦ የማብራት ስነ-ስርዓት እንደሚከናወን አባ ገዳ ፍቃዱ ይገልፃሉ። ከዚህ በተጨማሪ ወጣቶች ባህላዊ ጭፈራ ሲጫወቱ፤ አባቶች ደግሞ ለፈረስ ጉግስ ይሰባሰባሉ በማለት የመስቀል በዓል የአከባበር ሁኔታውን ይገልፃሉ።

‎አባ ገዳ ፍቃዱ እንደሚያስረዱት፤ ባህላዊ ጨዋታ ወጣቶች ወጣትነትን እና ጀግንነትን የሚያሳዩበት ሲሆን አባቶች ደግሞ የዛ ወኔ ተካፋይ ስለሆኑ የፈረስ ጉግስ እንደሚያሳዩ ተናግረዋል። በፈረስ ጉግስ ውድድር ጀግና ወይም ጎበዝ የሆነ ፈረስ ያለው አባ ዳማ ወይም አባ ቡሎ በመባል ይሰየማሉ ብለዋል። ስያሜውን የሚያገኙት፤ ፈረስ የሚጋልበው አባወራ ስማቸው ዳማ ወይም ቡሎ ከሆነ አባ ዳማ ወይም አባ ቡሎ የሚሉ ስያሜዎችን እንደሚያገኙ ተናግረዋል።

‎የመስቀል በዓል አከባበር እንደየአከባቢው ባህል እና ወግ በተለያዩ ሁነቶች ሲከበር፤ በቱለማ እና አካባቢው በዚህ መልኩ በድምቀት ይከበራል።

‎በሔለን ተስፋዬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review