መስቀል በቤተ-ጉራጌ

You are currently viewing መስቀል በቤተ-ጉራጌ

AMN – መስከረም 14/2018 ዓ.ም

የመስቀል በዓል የክርስትና መሠረት ከሆነው የክርስቶስ መስቀል መገኘት ጋር ተያይዞ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚከበር በዓል ነው፡፡

የመስቀል ደመራ በዓል በ2006 ዓ/ም በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበ ሲሆን፤ ይህም ከሀገራችን አልፎ በሌሎች ሀገራት ልዩ ስፍራ እንዲሰጠውና የቱሪስት ፍሰት እንዲጨምር አድርጓል ፡፡

በሃገራችን የመስቀል በዓል የሚያከብሩ አካባቢዎች ላይ የሚኖሩ ብሄር ብሄረሰቦች እንደ አኗኗር፣ ወግ እና ልማዳቸው በተለያዩ ዝግጅቶች ያከብሩታል፡፡

በቀድሞው የደቡብ ክልል በአሁኑ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ብሄር ብሄረሰቦች መካከል አንዱ በሆነው የጉራጌ ብሄረሰብ በዓሉ እንዴት ይከበራል?

ነዋሪነታቸውን በአዲስ አበባ ከተማ ያደረጉት የብሄረሰቡ ተወላጅ ወ/ሮ ገነት ስዩም ከኤ ኤም ኤን ዲጂታል ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የመስቀል በዓል በሀገር አቀፍ ደረጃ መስከረም 16 እና 17 ቀን የሚከበር ቢሆንም፤ በጉራጌ ብሄረሰብ ግን ከመስከረም 12 እስከ ጥቅምት 5 ድረስ ይከበራል፤ ለዚህም ከሶስትና አራት ወራት በፊት የበዓል ዝግጅቱ ይጀመራል ነው ያሉት፡፡

በቤተ-ጉራጌ መስከረም 12 ቀን የመመገቢያ ቁሳቁሶች ከተሰቀሉበት የሚወርዱበትና ፀድተው እስከ ጥቅምት 5 ቀን ለምግብ ማቅረቢያነት አገልግሎት እንዲሰጡ የሚዘጋጁ ሲሆን፤ ይህ ቀን በብሄሩ አጠራር ሌማት ይወርድቦ በመባል ይታወቃል፡፡

መስከረም 13 ቀን ወሬት የኸና ይሉታል ቤተ-ጉራጌዎች፤ ትርጉሙም እንቅልፍ ከልካዩ ቀን በመባል ይታወቃል፤ ቀኑ የጐመን ክትፎ የሚዘጋጅበትና የሚበላበትም ሲሆን፤ በዚህ ቀን በተለይ ሴቶች የሚጠግቡበት ነው፡፡ ሴቶች ቀጣዮቹን የበዓላት ቀናት እንግዶችን በማስተናገድ በስራ ስለሚያልፉ ይባላል፡፡

መስከረም 14 ቀን በብሄሩ አጠራር ደንጌሣት ይባላል የልጆች ደመራ ወይም እሳት ማለት ነው፡፡ በዚህ ዕለት ማታ ሁሉም በየደጃፉ ትንንሽ ደመራ በመለኮስ ልጆች ባህላዊ ጭፈራዎችን በመጨፈርና ሴቶች ደግሞ በእልልታ ለቀኑ ስላደረሳቸው ፈጣሪያቸውን ያመሰግናሉ፡፡

መስከረም 15 ወኸመያ ወይም ጨርቆስ ይባላል አመት በዓል የሚል ትርጉም አለው፤ ዋናው የመስቀል በአል የሚከበርበትና እርድ የሚፈፀምበት ቀን እንደሆነ ወ/ሮ ገነት ይገልፃሉ።

መስከረም 16 ደመራ የሚቃጠልበት ቀን ሲሆን በዚህ ዕለት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተሳትፎ የሚያደርግበት የደመራ በአል ይከናወናል፡፡ ቀኑን አዳብና ይሉታል ይህ ዕለት ሴትና ወንድ ወጣቶች በአደባባይ የሚገናኙበት፣ የሚጨፍሩበትና ለጋብቻ የሚተጫጩበት ነው፡፡

በዚህ ቀን የብሄረሰቡ መገለጫ የሆነውን እንደ ክትፎ፣ ቆጮ እና ሌሎች ባህላዊ ምግቦች እና መጠጦችን እየተመገቡና እየጠጡ ልዩ በሆነው የአጨፋፈር ስልታቸው እየተጫወቱ በዓሉን በደማቅ ሁኔታ ያከብሩታል፡፡

መስከረም 17 ንቅባር ወይም የከሰል ማይ ይሉታል የከሰል ቀን ማለት ነው፡፡ በዚህ ቀን ከማለዳው 12 ሰአት ጀምሮ በአንድ አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎች ደመራው ወደ ተቃጠለበት ቦታ በመሄድ የአካባቢያቸውን የዕድር ዳኛ በመቀየር አዲስ የሚመርጡበትና ክፉ ነገር ላለመስራት ቃለ መሃላ የሚፈፀምበት እንዲሁም ፈጣሪን የሚያመሰግኑበትና ለመጪው ጊዜ መልካም ምኞት የሚመኙበት ቀን ነው፡፡

በዚህ እለት ጐጆ የውጡ ወንድ ልጆች የዕድር አባልነት ጥያቄ በማቅረብ ምዝገባ የሚፈቀድበትም ቀን መሆኑንም ነው ወ/ሮ ገነት የገለጹት፡፡

መስከረም 18 የመስቀል ዝግጅት እየተገባደደ ሄዶ በብሄሩ አጠራር የፌቃቆማ ተብሎ ይጠራል ትርጉሙም የስንደዶ ለቀማ ቀን ማለት ነው፡፡ የስንደዶ ለቀማው በባህላዊ ዜማዎች ታጅቦ በልጃገረዶች ይከናወናል።

በቤተ ጉራጌ ከመስከረም 17 እስከ 23 የዘመድ መጠየቂያ ጊዜ ሲሆን የጀወጀ ወይም የጀመቸ ተብሎ ይጠራል።

በዚህ ጊዜ በክረምቱ ተለያይቶ የኖረ ቤተ-ዘመድ የሚገናኙበት፣ ማህበራዊ ችግሮቻቸውን የሚፈቱበት፣ ወጣቶች የሚተጫጩበትና ራሳቸውን ለጋብቻ የሚያዘጋጁበት፣ የሞቱ ሰዎች ለቅሶ የሚደረስበት፣ አልፎ አልፎም በጥል የተለያዩ ባልና ሚስቶች የሚታረቁበት አጋጣሚ ይፈጠራል፡፡

እንዲህ እያለ በቤተ-ጉራጌ የመስቀል በዓል እስክ ጥቅምት 5 ቀን ድረስ ዘልቆ በዚህ ቀን መስከረም 12 የወረደው የመመገቢያ ዕቃ ወደነበረበት ተመልሶ ሁሉም ተመራርቆ ወደየመጣበት ይመለሳል ነው ያሉት ወ/ሮ ገነት ፡፡

የጉራጌ ብሄረሰብ የመስቀል በዓልን፤ የበዓላት ሁሉ አውራ አድርጐ ለአመታት ሲያከብር፤ ከሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ትውፊቱ ባሻገር ለማህበራዊ እሴቱና ፋይዳው ትልቅ ግምት በመስጠት ነው፡፡

በ-በረከት ጌታቸው

#Culture

#holiday

#Ethiopia

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review