የመስቀል በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ ለሌሎችም የአደባባይ ክብረ በአላት የሚያደርገዉን ድጋፍ የከተማዉ አስተዳደር እያደረገ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ፡፡
የኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ፓትሪያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ስራ አስኪያጅ ብፁእ አቡነ ሳዊሮስ ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ ብፁህ አቡነ ዲዎስቆሮስ እንዲሁም የአ/አ አገረ ስብከት ሊቀ ዻዻስ ብፁህ አቡነ ህርያቆስ እና የመስቀል በአል አዘጋጅ ኮሚቴ በተገኙበት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እና ከከተማዉ አስተዳደር የስራ ኃላፊዎች ጋር በበአሉ ቅድመ ዝግጅት እና በከተማዉ አስተዳደር ስለሚደረገዉ ድጋፍ ዙሪያ ተወያይተዋል።

የመስቀል ደመራ በአል መስቀል አደባባይን ጨምሮ በ 2 ሺህ 375 ደብሮችና ቦታዎች ላይ የሚከበር መሆኑን በመጥቀስ ሃይማኖታዊ ቱፊቱን እና ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ በደመቀና ባማረ መልኩ እንዲከበር የከተማዉ አስተዳደር ከማእከል እስከ ወረዳ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን በመግለፅ አባቶች እና የኮሚቴዉ አባላት እየተረገ ላለዉ ድጋፍ ምስጋናቸዉን አቅርበዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዉይይቱ የበአሉ ዋና ባለቤትና በአሉን የምትመራዉ ፣ የምታስተባብረዉ የኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ ብትሆንም የመስቀል ደመራ በአል ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝብ በአደባባይ የሚያከብረዉ የአገር ሀብት ፣የከተማችን ድምቀት ፣ የቱሪዝም መስህብ ነዉ ያሉ ሲሆን፤ ሃይማኖታዊ ቱፊቱን እና እሴቱን በጠበቀ መልኩ በድምቀት እንዲከበር፣ አብሮትን በሚያጠናክር መልኩ እና በሰላም እንዲጠናቀቅ ለሌሎችም የአደባባይ ክብረ በአላት የሚያደርገዉን ድጋፍ የከተማዉ አስተዳደር እያደረገ ይገኛል ማለታቸውን ከከንቲባ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡