በጉራጌ ዞን በሚከበረዉ የመስቀል በአል ላይ ከ887ሺህ በላይ የሃገር ዉስጥና የዉጭ ሃገር ቱሪስቶች ይሳተፋሉ

You are currently viewing በጉራጌ ዞን በሚከበረዉ የመስቀል በአል ላይ ከ887ሺህ በላይ የሃገር ዉስጥና የዉጭ ሃገር ቱሪስቶች ይሳተፋሉ

AMN – መስከረም 14/2018 ዓ.ም

በጉራጌ ዞን በሚከበረዉ የዘንድሮዉ የመስቀል በአል ላይ ከ887 ሺህ በላይ የሃገር ዉስጥና የዉጭ ሃገር ቱሪስቶች እንደሚሳተፉ የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ገለጸ፡፡

የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ ወ/ሮ መሰረት አመርጋ በተለይ ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዲጂታል ሚዲያ እንደተናገሩት፤ የመስቀል በዓል በጉራጌ ብሄር ተወላጆች በየአመቱ በተለያዩ ሃይማኖታዊና ባህላዊ መርሃ ግብሮች በድምቀት ተከብሮ ይዉላል፡፡

በዘንድሮዉ የመስቀል ደመራና የመስቀል በዓል ላይ ለመሳተፍም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የጉራጌ ብሄር ተወላጆችና እንግዶች ከሃገር ዉስጥና ከዉጪ ሃገራት ጭምር ወደ ዞኑ በመግባት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

ባለፈዉ አመት በዞኑ በተከበረዉ የመስቀል በአል ላይ ከ800 ሺህ በላይ የሃገር ዉስጥ እንዲሁም ከ 4ሺህ በላይ የዉጭ ሃገር ቱሪስቶች መሳተፋቸዉን የገለጹት ሃላፊዋ፤ በዘንድሮዉ የመስቀል በአል ላይ ከ887ሺህ በላይ የብሄሩ ተወላጆች፤ የሃገር ዉስጥ እና የዉጭ ሃገራት ቱሪስቶች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡

የብሄሩ ተወላጆችና እንግዶች በአሉን ለማክበር ወልቂጤን ጨምሮ ወደዞኑ ከተሞችና ወረዳዎች በሚሄዱበት ወቅት በመንግስት አመራሮችና በአካባቢዉ ማህበረሰብ ደማቅ አቀባበል እየተደረገላቸዉ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል፡፡

ታዳሚዎቹ በቆይታቸዉ በቤተሰብ ደረጃ በአሉን ከማሳለፋቸዉ በተጨማሪ በተለያዩ ፌስቲቫሎች ላይ እንደሚሳተፉ፤ የቱሪዝም ስፍራዎችን እንደሚጎበኙና በዞኑ እየተከናወኑ ባሉ የልማት ስራዎች ላይ የበኩላቸዉን እንደሚወጡም አስገንዝበዋል፡፡

እስካሁን ድረስም በርካታ የጉራጌ ብሄር ተወላጆች በተለያዩ የኢንቨስትመንት እና የልማት ስራዎች ላይ በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙም ሃላፊዋ ገልጸዋል፡፡

የመስቀል በዓል የጉራጌን ህዝብ ባህላዊ እሴቶችና የቱሪዝም መስህቦችን ከማስተዋወቁም በላይ ተጨማሪ የኢኮኖሚ ምንጭ በመሆን ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

በርካታ የዞኑ ነዋሪዎች ለባህላዊ ምግቦች ግብአት የሚሆኑ የግብርናና የእንስሳት ምርቶችን በማምረት፤ የተለያዩ የእደ ጥበብ ዉጤቶችን፤ የአልባሳትና የስፌት ስራዎችን በማዘጋጀት ተጨማሪ የስራ እድልና የገቢ በመፍጠር ላይ ይገኛሉ ያሉት ሃላፊዋ፤ እነዚህ ምርቶች ወደ ዉጪ ሃገራት ጭምር እንደሚላኩ ነዉ ያስገነዘቡት፡፡

የዘንድሮዉ የመስቀል በአል ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቱን በጠበቀ መንገድ በአብሮነት፤ በወንድማማችነትና በሰላም እንዲከበር ከአጎራባች ክልሎችና ዞኖች ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ ወ/ሮ መሰረት አመርጋ በተለይ ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዲጂታል ሚዲያ ተናግረዋል፡፡

ጉራጌ በኢትዮጵያ ከሚገኙ በርካታ ብሄር ብሄረሰቦች አንዱ ሲሆን፤ በስራ አክባሪነቱና ወዳድነቱ ይታወቃል፡፡ ክትፎና የጎመን ክትፎም ጉራጌ ከሚታወቅባቸዉ የባህል ምግቦች ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review