ኢትዮጵያ እና ኬንያ ከ62 አመታት በኋላ ወታደራዊ የትብብር ስምምነት ለሁለተኛ ጊዜ ተፈራርመዋል።
ዛሬ የተደረገው ስምምነት ኬንያ ነጻነቷን ባገኘችበት እ.ኤ.አ ዲሴምበር 1963 ከተፈራረሙ በኋላ ለ2ተኛ ጊዜ መከላከያ ለመከላከያ የተደረገ ታላቅ ወታደራዊ ስምምነት መሆኑም ተገልጿል።
ስምምነቱን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እና የኬንያ መከላከያ ኢታማዦር ሹም ጄነራል ቻርልስ ሙሪዩ ካሃሪሪ ተፈራርመዋል።
ሁለቱ ወገኖች በመከላከያ ጠቅላይ መምሪያ የሁለትዮሽ ውይይት ካደረጉ በኋላ ነው በጋራ መስራት በሚቻልባቸው መስኮች ወታደራዊ የትብብር ስምምነቱን የተፈራረሙት።
ወታደራዊ የትብብር ስምምነቱ ስትራቴጂካዊ በሆኑ ስራዎች ላይ በጋራ መስራት የሚያስችል ሀገራቱ በመካከላቸው ያለው ግንኙነትና መተማመን በሚያድግበት ወቅት የሚፈፀም ነው።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በወቅቱ እንዳሉት የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው የኢትዮጵያ እና ኬንያ መከላከያ ተቋማት በተለያዩ ወታደራዊ መስኮች ያላቸው ትብብር ተጠናክሮ ይቀጥላል።
ከኬንያ ጋር በጋራ ወታደራዊ ልምምድ፣ በወታደራዊ ኢንዱስትሪ፣ ሽብርተኝነትን በመዋጋት፣ በድንበር ደህንነት እና በሌሎችም ተያያዥነት ባላቸው ወታደራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ስምምነት ተፈራርመናል ማለታቸው ተገልጿል።
በስምምነቱም ከሀገራቱ በተጨማሪ በቀጣናው ሰላምና ደህንነት ላይ በጎ ተፅዕኖ የሚፈጥሩ በርካታ ስራዎችን አብረን እንሰራለን ብለዋል።
ለእርሳቸውና ለልዑካን ቡድናቸው ለተደረገላቸው ደማቅና የሞቀ አቀባበል ምስጋና ያቀረቡት ጄኔራል ቻርልስ ሙሪዩ ካሃሪሪ በበኩላቸው የኢትዮጵያ እና የኬንያ ግንኙነት ከታሪክ ባለፈ በባህል፣ ህዝብ ለህዝብ እና በጂኦግራፊ ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያና ኬንያ ያደረጉት ወታደራዊ ስምምነት ከሀገራቱ ባለፈ ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋትም የጎላ ፋይዳ እንዳለው ገልፀው፤ ከኢትዮጵያ መከላከያ ጋር በትብብር ለመስራት የኬንያ መከላከያ ቁርጠኛ መሆኑን እንዳረጋገጡ የመከላከያ ሰራዊት ሚዲያ ያደረሰን መረጃ ያመለክታል።