የአፍሪካ መዲና የሆነችዉ አዲስ አበባ በአዲሱ አመት ዋዜማ የተለያዩ አህጉር እና ዓለም ዓቀፍ ጉባኤዎችን በተሳካ መንገድ አስተናግዳለች።
ይህም አዲስ አበባን የኮንፍራንስና የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ በከተማ አስተዳደሩ የተያዘዉ ራዕይ እየተሳካ ስለመሆኑ አመላካች ነዉ።
ከ2018 ዓ.ም አዲስ ዓመት ጋር በተያያዘም በአሉ ፍጹም ሠላማዊ በሆነ መንገድ የተከበረ ሲሆን በወርሃ መስከረም የሚከበሩ ትላልቅ የአደባባይ በዓላትም ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴታቸዉን ጠብቀዉ እንዲከበሩ አስፈላጊዉ ቅድመ ዝግጅት ተጠናቋል።
የመስቀል ደመራ እና የኢሬቻ በዓላት በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የማይዳሰሱ ቅርሶች ሆነዉ በዩኔስኮ ከመመዝገባቸዉ ጋር እና ከተለያዩ የአለም ክፍሎች የሚመጡ ቱሪስቶች የሚሳተፉበት በአላት እንደመሆናቸዉ መጠን አለም አቀፍ ደረጃቸዉን ጠብቀዉ እንዲከበሩ ሰፊ ዝግጅት ተደርጓል።

የአዲስ አበባ ከተማ የቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ሁንዴ ከበደ ከኤኤምኤን 24/7 ጋር በነበራቸው ቆይታ ያረጋገጡትም በበአላቱ ላይ ለመታደም የሚመጡ ቱሪስቶች ደስተኛ ሆነው እንዲያሳልፉና የቆይታ ጊዚያቸውንም እንዲያራዝሙ እየተሰራ መሆኑን ነዉ።
በበዓላቱ ላይ ለመታደም የሚመጡ እንግዶችን በአግባቡ ማስተናገድ የሚችሉ እና ምቹ የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎች አዲስ አበባ ውስጥ ይገኛሉ ያሉት ኮሚሽነሩ የመስቀል ደመራ እና የሆረ ፊንፊኔ የኢሬቻ በዓል በመዲናዋ መከበሩ የከተማዋን ህብረብሄራዊነት ይበልጥ ከማጉላቱም በላይ የጎብኝዎችን ፍሰት የሚያሳልጡ መሆናቸውን ገልፀዋል ፡፡
ሰሞኑን በሚከበሩ የአደባባይ በአላት ላይ ለሚታደሙ ጎብኝዎች የተሻለና የተሳለጠ አገልግሎት ለመስጠት ከአስጎብኝ ድርጅቶች ጋር በትብብር እየተሰራ ነዉ።

ቦሌ ዓለም ዓቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን ጨምሮ በበርካታ የከተማዋ አካባቢዎች 24 ሰአት አገልግሎት የሚሰጡ ትልልቅ የመረጃ ማዕከላት መከፈታቸውንም አንስተዋል ፡፡
አገልግሎት ሰጭ ተቋማቱ በእነዚህ በዓላት ለሚመጡ ጎብኝዎች ከፍተኛ ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ያነሱት ኮሚሽነሩ በዓላቱ ተጀምረው አስኪጠናቀቁ ድረስ ህብረተሰቡ በተለመደው የእንግዳ ተቀባይነት ስሜት በማስተናገድ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
በያለው ጌታነህ