በድሬዳዋ ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሥራ ጀመረ

You are currently viewing በድሬዳዋ ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሥራ ጀመረ

AMN መስከረም 15/2018

በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የድሬ-መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተካሒዷል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር እናትዓለም መለሰ እና የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ከድር ጁሃርን ጨምሮ የተለያዩ አካላት ተገኝተዋል።

የድሬ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለህዝብ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል መሆኑን ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

መንግስት ለህዝብ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ዘመናዊ፣ ፈጣንና ቀልጣፋ ለማድረግ እያከናወናቸው የሚገኙ የሪፎርም ተግባራት በውጤታማነት መቀጠላቸውን አንስተው የመሶብ አንድ ማዕከልም የዚሁ ማሳያ ነው ብለዋል።

በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች የጀመሯቸውን የለውጥ ስራዎች አጠናክረው በማስቀጠል የህዝብን አገልግሎት አሰጣጥ በማሳለጥ በቁርጠኝነት፣ በቅንነትና በታማኝነት እንዲያገለግሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር በበኩላቸው ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ የህዝብ የዘመናት የአገልግሎትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በፍጥነትና በጥራት የመመለስ ስራ መሆኑን አንስተዋል።

በዚህም መሰረት አስተዳደሩ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ቀልጣፋ፣ ፈጣንና በቴክኖሎጂ የታገዙ አገልግሎቶችን ተደራሽ በማድረግ አበረታች ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

ዛሬ የተመረቀው የድሬ መሶብ የአንድ ማዕከል የአገልግሎት መስጫም የመንግሥት አገልግሎቶች በተቀናጀና በተናበበ ሁኔታ በግልፅነት፣ በፍጥነት መስጠት ያስችላል ብለዋል።

መሶብ ስማርት ድሬን እውን ለማድረግ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በድሬዳዋ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በመጀመሪያው ምዕራፍ ስድስት ተቋማትና 28 አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ በታገዘው አደረጃጀትና አሠራር ፈጣንና ቀልጣፋ ዘመናዊ አገልግሎቶች መስጠት መጀመራቸውን የተናገሩት ደግሞ የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ ናቸው።

ለተቋማቱ የዘመኑን አገልግሎት መስጠት የሚችሉ 64 ባለሙያዎች ስልጠና ወስደው ወደ ስራ መግባታቸውንም ተናግረዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review