የመዲናዋን ሰላም አስተማማኝና ዘላቂ ለማድረግ ከኤ ኤም ኤን ጋር በትብብር እንደሚሰራ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ

You are currently viewing የመዲናዋን ሰላም አስተማማኝና ዘላቂ ለማድረግ ከኤ ኤም ኤን ጋር በትብብር እንደሚሰራ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ

AMN – መስከረም 15/2018 ዓ.ም

የመዲናዋን ሰላም አስተማማኝና ዘላቂ ለማድረግ ከኤ ኤም ኤን ጋር በትብብር እንደሚሰራ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አስታውቋል፡፡

የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋን ጨምሮ የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ዋና መስሪያ ቤትን ጎብኝተዋል፡፡

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ወንጀልን ለመከላከል የሚደረጉ ጥረቶችን እና በከተማዋ ውስጥ የሚከናወኑ ሁሉን አቀፍ ልማቶች ከህዝብ ዘንድ በማድረስ አበረታች ስራ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ደመላሽ ገ/ሚካኤል ገልፀዋል፡፡

ኮሚሽነር ደመላሽ ገ/ሚካኤል፤ ፌዴራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ስራዎችን ጥራቱን በጠበቀ መልኩ እያከናወነ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም ታላላቅ ህዝባዊ እና ሃይማኖታዊ በዓላት እንዲሁም ሌሎች በርካታ ዜጎች የሚሳተፉባቸው መድረኮች በሰላም እንዲጠናቀቁ አስችሏል ብለዋል፡፡

አዲስ አበባ የኮንፈረንስ ማዕከልነቷ እየጨመረ መምጣቱን እና የአለም የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷም የበለጠ እያደገ መምጣቱን ተከትሎ፤ ከዚህ ተግባር እና እንቅስቃሴ ጋር የሚመጣጠን የወንጀል መከላከል ስራ እየተሰራ መሆኑን እና በዚህም አዲስ አበባን ደህንነታቸው አስተማማኝ ከሆኑ ከተሞች ተርታ ማስቀመጥ መቻሉን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡

ተቋሙ ያከናወነው ሪፎርም ተልዕኮዎችን በብቃት ለመወጣት እንዳስቻለው የጠቆሙት ኮሚሽነሩ፤ ዓለም የደረሰበትን ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች በመታጠቅ ወንጀል የመከላከል እና ሰላም የማስጠበቅ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡

የተገኙ ውጤቶችን የማስቀጠል እና የበለጠ ውጤታማ የማድረግ ስራም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

በመጪዎቹ ጊዜያት የሚከበሩት የመስቀል እና የኢሬቻ በዓላት ሃይማታዊ እና ባህላዊ እሴታቸውን በጠበቀ መልኩ እንዲከበሩ አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን እና ለዚህም ይረዳ ዘንድ ከማህረሰቡ ጋር በመቀናጀት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ፌዴራል ፖሊስ ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችል ውይይት መደረጉን የጠቆሙት ኮሚሸነር ደመላሽ፤ የጸጥታ ስራው ከህረተሰቡ ጋር ለማገናኘት በሚደረገው ጥረት በርካታ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይ ከሚዲያ ተቋሙ ጋር የሚኖረው ግንኙነት የተጣናከረ እንደሚሆን የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ ተቋሙ ህዝብን እና መንግስትን በማገናኘት ረገድ ያከናወናቸውን አበረታች ስራዎች አጠናክሮ መቀጠል እንደሚኖርበትም ጠቁመዋል፡፡

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ሰፊ አድማስ ያለው በመሆኑ ከተቋሙ ጋር በጋራ ለመስራት ያላቸውን ዝግጁነትም አጽንዖት ሰጥተዋል፡፡

የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ፤ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በቴክሎጂ እና ሰው ኃይል ትልቅ ለውጦችን ያመጣ መሆኑን ገልጸው ኤ ኤም ኤን ለሚያከናውናቸው ሪፎርሞች ጥሩ ግብዓት መሆኑን አብራተዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ያከናወነው የሪፎርም ስራ ውጤታማ እና ትልቅ ተሞክሮ የሚወሰድበት መሆኑን የገለጹት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ ኤ ኤም ኤን በየጊዜው እራሱን እያሳደገ ያለ እና ተመራጭ እየሆነ የመጣ የሚዲያ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ በኢትዮጵያ ከሚያከናውናቸው ስራዎች በተጨማሪ በአዲስ አበባ ከተማ ተጨባጭ እና ውጤታማ ስራን እያከናወነ መሆኑን የገለጹት አቶ ካሳሁን፤ ኤ ኤም ኤን ፌዴራል ፖሊስ የሚያከናውናቸውን ስራዎች ከህዝብ ዘንድ በማድረስ ኃላፊነቱን እንደሚወጣም ተናግረዋል፡፡

በአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ እና የፌዴራል ፖሊስ በቀጣይ በመቀራብ እና በመቀናጀት ለመስራት የሚያስችል ውይይት መካሄዱ የተጠቀሰ ሲሆን ተቋሙ በቴሌቪዥን፣ ራዲዮ፣ ህትመት እና ዲጂታል በአምስት የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች እና ሁለት ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ወደ ተደራሲው እየደረሰ መሆኑም ተመላቷል፡፡

በሃብታሙ ሙለታ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review