በቆይታ ወይም በረዥም ግዜ ብቅ ለሚሉ ወዳጆች ምነው እንደመስቀል ወፍ አልፎ አልፎ ብቅ ትላለህ ይባላል።
ይህ ብቻ አይደለም እንደ መስቀል ወፍ የሚወዱት ሰው ከአይናቸው ሲሰወር እንዲህ እያሉም ይዘፍናሉ።
የመስቀል ወፍ እና አንቺ ልጅ ያው ናችሁ በአመት አንዴ በቻ ብቅ ትላላችሁ …………
በድምፃዊው ሰማህኝ በለው ከተዜመው ስንኞች ውስጥ የተወሰደ የዘፈን ግጥም ነው ። በዚህ ግጥም በዓመት አንዴ ላያት እንስት የተዜመ ነው።
”መስቀል ወፍ እና የአደይ አበባ፣::

ቀጠሮ እንዳላቸው መስከረም ሲጠባ” እንዲል ገጣሚው የሁለቱን በወርሀ መስከረም ብቅ ማለታቸውን ይገልፃል ። አንድ ሰው ለረጅም ጊዜ ጠፍቶ ቆይቶ ድንገት ሲከሰት ‘ ምነው የመስቀል ወፍ ሆንክ’ ይባላል።
ይህም ለረጅም ጊዜ ሳይታይ ወይም ጠፍቶ ቆይቶ መታየትን ለማመልከት ማህበረሰቡ የሚጠቀምበት አባባል ነው። አእዋፋትን በቅርበት የሚያጠኑት ባለሞያዎችም ከዚህ አባባል ጋር ይስማማሉ ።
የመስቀል ወፍን በተመለከት የኤ ኤም ኤን ዲጅታል በኢትዮጰያ ብዝሀ ህይወት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር እና የእንስሳት ተመራማሪ ከሆኑት ተስፉ ፈንከሳ (ዶ/ር) ጋር ቆይታ አድርጓል።
የመስቀል ወፎች በኢትዮጰያ ብቻ የሚገኙ ናቸው? ነው ወይስ በሌሎች አገሮች ይገኛሉ በሚለው የብዙዎች ጥያቄዎች ላይ ምላሽ ሰጥተዋል ። የመስቀል ወፍ በኢትዮጰያ ብቻ ሳይሆን ከሌላ ቦታ የሚሰደዱ፤ በአፍሪካ በታችኛው የሰሃራ በረሃ አካባቢ በብዛት የሚገኙ መሆናቸውን ተመራማሪው ይጠቁማሉ ።

የእነዚህ አዕዋፋት ስያሜያቸው ዊዶ( widow bird)፣ ቢሾኘ (bishop)፣ ኢንዲጎ (Indigo) እና ዋይዳህ (whydah) የሚባሉ የወፍ ዓይነቶች በአንድ ላይ የመስቀል ወፍ በመባል እንደሚታወቁ አስረድተዋል ፡፡
የመስቀል ወፍ ከ10 በላይ ዝርያዎች ያሏቸው ሲሆን፤ እነዚህ የወፍ ዝርያዎች በመስከረም ወር መግቢያ ወቅታዊ መራቢያቸው በመሆኑ የፆታ ጓደኞቻቸውን ለመሳብ ሴቶቹ ቀለማቸውን እንደወቅቱ እንደሚቀያይሩም ይገልፃሉ፡፡
ለዚህም ነው በሀገራችን መስከረም ወር የተለያዩ ህብረ ቀለማት ያላቸው ወፎች ይከሰታሉ የሚሉት ተመራማሪው፣ ከዚህ በተጨማሪም የተወሰኑ ወፎች እንቁላሎቻቸውን በሌሎች የወፍ ጐጆዎች ሄደው በመጣልም ይራባሉ ብለዋል ፡፡
ብዙዎቹ ከጥቁር ውጭ ጠቆር ያለ ቡኒ እግሮች እንዳላቸው፣ ልዩነታቸውም መንቆራቸው እና እግሮቻቸው ላይ ነው በሚታየው ሲሉም ተናግረዋል ። የመስቀል ወፍ ዝርያዎች ግን በመጠን፣ በመንቆር፣ በላባቸው ቀለም እና በእግራቸው ቀለሞች ይለያያሉ። የመራባት ሁኔታ ላይ ግን በአንድ አካባቢ የሚኖሩ በተሻለ የመቀራረብ ዕድል እንዳላቸው ይገመታል።
የመስቀል ወፍ ተባዕቶቹ የወፎ ዝርያዎች የላባ ቀለም በመቀያየር እንስቶቹን የበለጠ በመሳብ የመራቢያ ወቅታቸው መምጣቱንና የሚያበስሩበት ወቅት መስከረም ወር አካባቢ መሆኑ ይገለፃል ፡፡
በአገራችንም ታዲያ በመስከረም ወር የወፍ ዝርያዎች የሚራቡበት ወርቃማ ጊዜ በመሆኑ የወፎቹ ዝማሬ ከአንፀባራቂ ቀለም ጋር ተያይዞ ወሩን የተለየ ትዝታ የሚፈጥሩበት ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በሔለን ተስፋዬ