የመስቀል አደባባይ፣ በዋናነት መጠሪያውን ያገኘው፣ በየዓመቱ መስከረም 16 ቀን የሚከበረው የደመራ በዓል የሚከናወንበት ቦታ በመሆኑ ነው።
መስቀል አደባባይ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ፣ በባህል እና በኪነ ጥበብ በርካታ ጉዳዮችን በማስተናገድ ብዙ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ሥፍራው በብዙዎች አዕምሮ ውስጥ በርካታ ትውስታዎችን የቀረጸ ነው፡፡
ከዓመታት በፊት አዲስ አበባን በሚመጥን መልኩ ነዋሪዎችም እንዲዝናኑበት ተደርጎ በከተማ አስተዳደሩ እድሳት ተደርጎለታል፡፡ በዚህም መስቀል አደባባይ ታድሶ ከዚህ ቀደም ከነበረበት ሁኔታ እጅግ አምሮና ደምቆ ሰኔ 6 ቀን 2013 ዓ.ም ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል፡፡
85 ሺህ 500 ስኩዌር ካሬ ሜትር ስፋት ያለው መስቀል አደባባይ፣ ከላይ የተለያዩ ሁነቶች የሚከናወኑበት ሥፍራ ሲሆን፣ ከስር ደግሞ የመኪና ማቆሚያ አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑን የኤግዚቢሽን ማዕከልና ገበያ ልማት ድርጅት የማርኬቲንግና ሽያጭ ሥራ አስኪያጅ አቶ ካሳሁን ድሪባ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡

የተሽከርካሪ ማቆሚያ ሥፍራው በአንድ ጊዜ 1 ሺህ 400 ተሽከርካሪዎችን ማቆም እንደሚያስችልም ይገልፃሉ፡፡ መስቀል አደባባይ የሚከለሉ ቦታዎችን ሳይጨምር ከ 2 ሚሊየን በላይ ሰው መያዝ እንደሚችልም ያብራራሉ፡፡
በመስቀል አደባባይ የደመራ ማብሪያው ቦታ ተለይቶ ያለ ሲሆን፣ ምንም ዓይነት ሁነት ሲከናወንም ሰዎች ወደ ሥፍራው እንዳይገቡ ተከልሎና ተጠብቆ እንደሚቆይ ይናገራሉ፡፡
የደመራ ማብሪያ ቦታው ምንም ዓይነት ኮንክሪት ሳይደረግበት በቀደመ ይዘቱ አፈር እንዳለ መቀመጡንም አቶ ካሳሁን አስረድተዋል፡፡
ብስክሌት መጋለብ፣ የተለያዩ መጫወቻዎች፣ የህብረት ስፖርት፣ በመስቀል አደባባይ ከሚከናወኑ በርካታ እንቅስቃሴዎች መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡
በ1993 ዓ.ም የተጀመረው “ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያም” ሲካሄድ የቆየው ጅማሬና ፍፃሜውን በዚሁ አደባባይ አድርጎ ነው።
በአደባባዩ ውጪያዊም ሆነ ውስጣዊ እንቅስቃሴዎች በተደራጀ መልኩ በደህንነት ካሜራ ቁጥጥር እንደሚደረግበትም ገልጸዋል፡፡
በታምራት ቢሻው