መስቀል ይቅር ባይነትን እና የተዳፈነ እውነትም እንደሚገለጥ የምንማርበት በዓል ነው ሲሉ የምዕራብ አርሲ ሀገረ ስብከት ስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊ መምህር ሀብተማሪያም ሰንደቅ ገልጸዋል፡፡
መምህር ሀብተማሪያም ሰንደቅ የመስቀልን በዓል በተመለከተ ሲያብራሩ፣ መስቀል ሰማይና ምድር፣ ሰው ከሰው፣ ነፍስ ከስጋ፣ ሰው እና እግዚአብሔር የታረቁበት፤ የራቀው የቀረበበት እና የጠፋው የተገኘበት ታላቅ በዓል ነው ብለዋል፡፡
በአጠቃላይ መስቀል ሰላም፣ ፍቅር እና አንድነት የታወጀበት ነው፡፡
በመስቀል ላይ የተከፈለው ዋጋ ለሰው ልጆች እና ለፍጥረት ሁሉ የተከፈለ መሆኑንም ያነሳሉ፡፡
ስለዚህም አንድ ሰው መስቀልን ሲያይ ከአምላኩ ያገኘውን ይቅርታ፣ የተቀበለውን ፍቅር እና የተከፈለለትን ዋጋ እንደሚያስብ በማንሳትም፣ ያንን መስቀል የተሸከመ ደግሞ የተደረገለትን ያደርጋል ብለዋል፡፡
የሰው ልጅና እግዚአብሔር የታረቁበት የጥል ግድግዳም የፈረሰበት መስቀል፣ የሰው ልጅም ያጣውን ልጅነት ዳግም ያገኘበት ነው ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ ይህ ሰላም፣ ፍቅር እና አንድነት የታወጀበትና ሰው ከአምላኩ የታረቀበት መስቀል፣ ዕውራንን በማብራት፣ አንካሳትን በመፍታት፣ ለምፃምን በማንፃት፣ ብዙ ተዓምራትን በማድረጉ የተገኘውን ምህረት እና ይቅርታ ያልተረዱ ሰዎች መሬት ውስጥ እንደቀበሩት ያወሳሉ ይላሉ፡፡
ነገር ግን ሰዎች የቀበሩት እውነትን ነበር ያሉት መምህር ሀብተማሪያም፤ ከሦስት መቶ ዓመታት በላይ ተቀብሮ ቆሻሻ እየተደፋበት በመቆየቱ ለጊዜው ተሳክቶላቸው ነበር ይላሉ፡፡
ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ እውነትን በሚፈልጉ፣ መስቀሉ በልባቸው ታትሞ በኖረ ሰዎች አማካኝነት ተፈልጎ ቆሻሻው ተጠርጎ፣ ተቆፍሮ ወጥቶ እውነት ለዓለም ብርሃን እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡
ይህም፣ መስቀል ለየት ብሎና ደምቆ እንዲከበር እንዳደረገው ይገልፃሉ፡፡
እውነት ብዙ ጊዜ ዋጋ ልታጣ፣ ልትገፋ፣ በላዩዋ ላይ ቆሻሻ የሚደፋ ሊኖሩ ይችላሉ ያሉት መምህሩ፤ ዋጋ ቢያስከፍልም ኋላ ላይ ግን መውጣቷ እንደማይቀርም ነው ያስረዱት፡፡
በመሆኑም ህዝበ ክርስቲያኑ መስቀልን ሲያከብር በመስቀሉ ያገኘውን ሰላም፣ ፍቅር፣ ይቅርታ እና ርኅራሄን ለሌሎች እያደረገ ሊሆን እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡
በታምራት ቢሻው