የመስቀል ደመራ በዓል ታሪካዊ ዳራ

You are currently viewing የመስቀል ደመራ በዓል ታሪካዊ ዳራ

AMN – መስከረም 15/2018 ዓ.ም

በኢትዮጵያ በአደባባይ ከሚከበሩ በዓላት መካካል የመስቀል ደመራ በዓል አንዱ ነው፡፡ ይህ በዓል ለምን እንደሚከበርና አጠቃላይ ያለውን ሀይማኖታዊ እና ማህበራዊ ፋይዳ በተመለከተ ኤም ኤን ዲጂታል በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ላምበረት ደብረ አረጋዊ ቤተ-ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል ክፍል ሀላፊ ከሆኑት ከመርጌታ ይርጋ አያሌው ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

እየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ከሀጢያታቸው ለማዳን እና ወደ ቀደመ ክብራቸው ለመመለስ ከመሰቀሉ በፊት፣ መስቀል የውንብድና እና ከፍተኛ ወንጀል የሠሩ ሰዎች ብቻ ይሰቀሉበት እንደነበር መርጌታ ይርጋ አያሌው አብራርተዋል፡፡

ነገር ግን ይላሉ መርጌታ ይርጋ፣ ከጌታችን መድሃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ስቅለት በኋላ መስቀል የመዳን ምልክት እና አርማ ሆኗል ፡፡

ጌታችን መድሃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል ከእርገቱ በኋላም በእየሩሳሌም በርካታ ተአምራትን ይሰራ ስለነበር፣ በዚህ ያልተደሰቱ የእየሩሳሌም ሰዎች፣ መስቀሉን ከሰዎች እይታ ለመሠወር ሲባል ጉድጓድ ቆፍረው ቀብረውት ነበር ይላሉ መርጌታ ይርጋ፡፡

መስቀሉ በተቀበረበት ቦታ የሚገኙ የእየሩሳሌም ነዋሪዎች በየቀኑ ቆሻሻ ስለሚጥሉበት ቦታው ወደ ተራራነት እየተቀየረ መምጣቱንም መርጌታ ይርጋ አብራርተዋል፡፡

በሰባ ዓመተ ምሕረት በኢየሩሳሌም ላይ በተደረገው ወረራ ምክንያት እየሩሳሌም ስለጠፋች እና በዚያ የነበሩ ክርስቲያኖችም በመሰደዳቸው፣ መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ የሚያውቅ ባለመገኘቱ ከ300 ዓመታት በላይ በቆሻሻ ክምር ስር ተቀብሮ እንደቆየም አንስተዋል፡፡

በ326 ዓ.ም ክርስቲያኖችን የሚደግፍ መንግስት በመንገሱ ምክንያት፣ የንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት እሌኒ ቅዱስ መስቀሉን ለመፈለግ ወደ እየሩሳሌም ጉዞ እንዳደረገች እና እዚያም ከደረሰች በኋላ ጉብታ የሆነውን ቦታ ሁሉ ብታስቆፍር መስቀሉ ያለበትን ቦታ ግን ማግኘት አልቻለችም፤ ሰውም ብትጠይቅ የሚያውቅ አልተገኘም ነበር ይላሉ መርጌታ ይርጋ፡፡

በርካቶች መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ ለማሳየት ፈቃደኛ ባይሆኑም፣ ንግስት እሌኒ ባደረገችው ጥረት ኪራኮስ የተባለው አይሁዳዊ፣ መስቀሉ የሚገኝበትን የጎልጎታን ኮረብታ እንዳመለከታት መርጌታ ይርጋ ተናግረዋል፡፡

ሆኖም ግን ኪራኮስ፣ ዘመኑ ከመርዘሙ ጋር ተያይዞ በአካባቢው ከነበሩት ከሦስቱ ተራሮች መካከል መስቀሉ የሚገኝበትን ትክክለኛ ቦታ ለይቶ ማወቅ እንዳልቻለም አንስተዋል፡፡

ኪራኮስም “አንቺም በከንቱ አትድከሚ፤ ሰውንም አታድክሚ፤ እንጨት በመሰብሰብ እጣን አፍሽበት፤ በእሳትም አያይዢው፤ የእጣኑ ጢስ ወደ ላይ ወጥቶ ወደ ታች ሲመለስ አቅጣጫውን አይተሽ አስቆፍሪው፤ በዚህ ምልክት ታገኚዋለሽ” አላት፤ እርሷም ያላትን ሁሉ አደረገች ብለዋል።

ንግሥት እሌኒም ከሦስቱ ተራሮች የቱ እንደሆነ ለመለየት በእግዚአብሔር መልአክ እርዳታ መስከረም 16 ቀን ደመራ አስደምራ ብዙ እጣንም በመጨመርና በማቃጠል ጸሎት ተያዘ የሚሉት መርጌታው፣ የእጣኑ ጢስ ወደ ሰማይ በመውጣት በቀጥታ ተመልሶ መስቀሉ ባለበት ተራራ ላይ በማረፉ እና በመስገዱ መስቀሉ ያለበትን ትክክለኛ ስፍራ እንዳመላከተም አብራርተዋል፡፡

በዚህም መሠረት መስከረም 17 ቀን የተጀመረው ቁፋሮ እስከ መጋቢት 10 ቀን ድረስ ለቆፋሪዎች ከፍተኛ ማበረታቻ እየተደረገላቸው ሌሊትና ቀን ለሰባት ወራት ያህል የጉድፍን ኮረብታ ቆፍረው ቆሻሻውንም ካስወገዱ በኋላ፣ ሦስት መስቀሎች መገኘታቸውን የሚያብራሩት መርጌታ ይርጋ፣ ከተገኙት ሶስት መስቀሎች መካከል ጌታችን እየሱስ ክርስቶች የተሰቀለበት መስቀል ህሙማንን በመፈወሱ እና ሙታንንም በማስነሣቱ ተለይቶ እንደታወቀ አብራርተዋል፡፡

የመስቀል ደመራ በዓል በኢትዮጵያ መከበር የተጀመረው ንግሥት እሌኒ ለመስቀሉ ቤተ-መቅደስ አሰርታ፣ እንዲቀመጥ ያደረገችበትን መስከረም 17 ቀን መሰረት በማድረግ እንደሆነም መርጌታ ይርጋ ድርሳናትን አጣቅሰው ገልፀዋል ፡፡

እንደ መርጌታ ይርጋ አያሌው ገለፃ፣ ደመራ የሚለው ቃልም ደመረ፣ ጨመረ፣ አንድ አደረገ፤ ከሚለው የግዕዝ ቃል የተወሰደ እንደሆነና መቀላቀልን፣ መገናኘትን፣ መሰብሰብን፣ አንድነትን እና ኅብረትን የሚያመላክት ነው ይላሉ፡፡

መዚህም መሰረት በሀገራች በየ አመቱ መስከረም 16 ቀን ሰዎች በየአካባቢያቸው በመሰባሰብ እና በተመባበር እንደ አቅማቸው ያላቸውን በማዋጣት ደመራ ይደምራሉ፣ በተደመረው ደመራ ዙሪያም በመሰባሰብ ደስታቸውን ይገልፃሉ፣ የተደመረውን ደመራም ለኩሰው ያበራሉ ይላሉ መርጌታ ይርጋ፡፡

የመስቀል ደመራ በዓል በአሁኑ ጊዜ ከሀይማኖታዊ ትውፊቱ ባለፈ፣ ከፍተኛ የቱሪስት መዳረሻ እየሆነ መምጣቱን የሚገልጹት መርጌታ ይርጋ፣ የመስቀል ደመራ በዓል በተባበሩት መንግስታት የሳይንስ፣ የትምህርት እና የባህል ድርጅት (በዩኔስኮ) በማናይዳሰሱ ቅርሶች ከተመዘገቡ ቅርሶች መካከል አንዱ ነው ፡፡

መስቀል የሰላማችን እና የድኅነታችን፣ የመቀደሳችን ዓርማ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጆች ለማዳን የዘላለም ሕይወትን ለመስጠት መስዋዕትነት የከፈለበት፣ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ያፈሰሰበት በመሆኑ፣ አምላካችንን የምንመለከትበት መስታወት እንደሆነም ነው መርጌታ ይርጋ ያብራሩት፡፡

የመስቀል ደመራ በዓልን ስናከብር አዲሱ አመት ለሀገራችን ህዝቦች የብልፅግና፣ የሰላም፣ የአንድነት፣ የፍቅርና የመተሳሰብ ዘመን እንዲሆን መርጌታ ይርጋ አያሌው ምኞታቸውን ገልጻዋል፡፡

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review