ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ከተሞችም መልክና ልክ፣ ማንነትና ዕውነት አላቸው፡፡ የከተማ ልማት ባለሙያዎች ሲንጋፖርን ሁሉን አቀፍ ከሆነ ጠንካራ የሀገረ መንግስት ግንባታ፣ ሞንትሪያልን በቋንቋ ብዝሃነት፣ ሆንግ ኮንግን ከንግድ እንቅስቃሴ፣ ቤጂንግን በፖለቲካ ማዕከልነት፣ ኦክስፎርድን ከትምህርት፣ ኒው ዮርክን ከብዙዎች ምኞትና ከምቾት የተዋደዱ ከተሞች ናቸው ይላሉ፡፡
በርግጥም ሁሉም ከተሞች እንደ ስሪታቸው፣ እንደ ታሪካቸው እና እንደ ዕጣ ፋንታቸው የራሳቸው ማንነት እንዳላቸው የከተማ ልማትና ፖለቲካል ሳይንስ ተመራማሪዎቹ ፕሮፌሰር ዳንኤል ኤ. ቤል እና አቨነር ዴ ሻሌት የከተሞች መንፈስ (The Spirit of Cities: Why the Identity of a City Matters in a Global Age) በሚል ርዕስ ፕሪንስተን ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ እ.ኤ.አ 2011 ባሳተመው ጥናታዊ መፅሐፋቸው ላይ አስፍረውታል።
ዋና መቀመጫውን ኒው ዮርክ ከተማ ያደረገው ዓለም አቀፉ የበይነ መረብ ሚዲያ ተቋም “Youth Journalism International” እ.ኤ.አ ታህሳስ 15 ቀን 2020 “Diversity and wonder in Addis Ababa” በሚል ርዕስ ባስነበበው መጣጥፍ አዲስ አበባን ብዝሃነት ጎልቶ፣ ደምቆና ፈክቶ የሚታይባት ‘የሁሉም ቤት’ የሆነች ከተማ በማለት ገልጿታል፡፡
እ.ኤ.አ ጥር 2021 “Cities and Identities” በሚል ርዕስ በታተመ መፅሐፍ እንደሰፈረውም የከተሞች ውበት ከማንነታቸው ይመነጫል፡፡ ከተሞች የማይደበዝዝ ውበት፣ የማያልቅ ቁንጅና እንዲሁም እንደ መስታወት ሁሉንም በልኩ የሚያሳይ ገፅታ ይኖራቸው ዘንድ የነዋሪዎቻቸውን ባህልና ማንነት ማክበር፣ ሁሉም እንደ እምነቱ፣ ባህሉና ወጉ ዘና የሚልባቸው ሳሎኑ፣ አረፍ የሚልባቸው መኝታ ቤቱ ሲያሻውም የሚቦርቅባቸው መስኩ መሆን እንዳለባቸው ተመላክቷል።
በርግጥም አዲስ አበባ ህብረ ብሔራዊነት ከፍ ብሎ የሚታይባት፣ ብዝሃ ባህል እንደ ከዋክብት የሚደምቁባት፣ የሁሉም ቤት የሆነች ከተማ መሆኗን ለማረጋገጥ ከነሐሴ አጋማሽ እስከ መስከረም ማብቂያ የሚከበሩ እንደ መስቀልና ኢሬቻ ያሉ የአደባባይ በዓላትን መመልከት በቂ ነው፡፡

በተለይም በደማቁ የመስከረም ወር የሚከበሩት የመስቀልና የኢሬቻ በዓላት ለአዲስ አበባ እንደ አደይ አበባ አሊያም እንደ መስቀል ወፍ ተናፋቂዎች ናቸው፡፡ በዓላቱ በሚከበሩበት ወቅት እንደ ዐባይ ወንዝ ከብዙ ማንነቶች የመነጨ ውበት በህብረ ቀለማት ተሸምኖ በየጎዳናዎቹ ሰላምና ደስታን እየዘራ ይገማሸራል፡፡
ወዲህ ደግሞ እንኳን ተኳኩላ ሹርባ ተሰርታ፣
ልቤ ፍስስ ይላል ቤቷን ያየሁ ለታ፡፡
እንዲል የሀገሬ ኮበሌ አዲስ አበባ መንገዶቿ በመልክ በረድፉ ተሰድረው፣ ሕንፃዎቿ ልክ እንደ ሙሽራ ቀልብን በሚገዙ ቀለማት ተኩለው፣ መናፈሻዎቿ ሰፍተውና ፋፍተው፣ ቀበናን የመሳሰሉ ወንዞቿ ፀድተውና ወዝተው፣ የመስቀል አደባባይን የመሳሰሉ የበዓላት ማድመቂያ ስፍራዎች እንደ አደይ አበባ አጊጠው፣ እንደ መስቀል ወፍ ተሸቀርቅረው፣ እንደ ንጋት ሐይቅ በራስ አቅምና እውቀት እንዳሻቸው ተንጣለው በኮሪደር ልማቱ ብርሃን ከዘመን ጋር እኩል በተገለጡበት ወቅት የሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓል በርግጥም ልዩ ነው፡፡
ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ቆይታ ያደረጉት በቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪዝም ፕሮሞሽን መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተሾመ ተክሉም ከላይ በጠቀስናቸው ሀሳቦች ይስማማሉ፡፡ መስቀልና ኢሬቻን የመሳሰሉ የአደባባይ በዓላት በቱሪዝሙ ከፍታ ላይ ትልቅ ሚና አላቸው፡፡ በዓላቱ በዓመት አንዴ ወይም ሁለቴ የሚከበሩ በመሆናቸው ተናፋቂነታቸው ይጨምራል፡፡
ከዚህም ባሻገር መቼ፣ እንዴትና የት ይከበራሉ? የሚለው ጉዳይ በቱሪስቶች ዘንድ ቀድሞ የሚታወቅ ነው የሚሉት አቶ ተሾመ፣ በዚህ መሰረትም የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ጎብኝዎች በበዓላቱ ለመታደም ቀደም ብለው ያቅዳሉ፡፡
በዓላቱን አስታከውም የተለያዩ ቦታዎችን መጎብኘት የሚያስችላቸውን ፓኬጅ ይገዛሉ፡፡ ከተለያየ ማንነትና አካባቢ በአንድ ስፍራ የተሰባሰቡ እና በልዩ ልዩ አልባሳት ያጌጡ ኢትዮጵያውያን ከጎብኝዎቻቸው ጋር በአንድ ልብና መንፈስ ሲደሰቱ ማህበራዊ መስተጋብራችንን የበለጠ ያጣምሩታል፤ ያሳድጉታል፤ ያጣፍጡታል፡፡ በዓለም መድረክ ያለንንም በጎ ስም በደማቁ ይፅፉታል ይላሉ አቶ ተሾመ ተክሉ፡፡
እንደ መስቀል ያሉ በዓላት በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የ????? ???? ???? (UNESCO) ?????? ?????? ????????? ???? ??? ?? ?? ??? ??? ????ሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) የተመዘገቡ በመሆናቸው ከኢትዮጵያውያን አልፈው የሰው ልጅ ሁሉ የጋራ ሀብት ሆነዋል። ይህንንም ተከትሎ እንደ መስቀል ያሉ በዓላት ሲከበሩ የዓለም ዐይንና ልብ ወደ ኢትዮጵያ ያማትራል፡፡
በዚህ ላይ ደግሞ አዲስ አበባ ለአደባባይ በዓላት የበለጠ ምቹ ሆናለች። የመስቀል በዓልን ደግሞ የኃይማኖቱና የእሴቱ ባለቤት ከሆኑት ባሻገርም ሁሉም በጉጉት ይጠብቀዋል፡፡ ስለሆነም ዛሬ ላይ ሆነን የመስቀል ደመራን፣ የአዲስ አበባን ማራኪ ውበት እና ቱሪዝምን ስናስብ ከፍ ባለ ሞራልና አቅም ነው፡፡

ቱሪዝም ቢዝነስና መዝናኛዎችን የያዘ ነው የሚሉት አቶ ተሾመ መዝናናት ደግሞ ዐይንም፣ ልብም፣ ቀልብም እኩል የሚደሰቱበት ነው፡፡ በመሆኑም መዝናናትን ስናስብ ዐይንም፣ ልብም እንዲሁም ዐዕምሮም ሰብሰብ ብለው ጥሩ ነገር የሚያዩበት፣ የሚያስቡበት እና የሚደሰቱበት ነው፡፡ አዲስ አበባም ደግሞ ለዚህ ምቹ ሆናለች፡፡
ከተማዋ አሁን በጣም የለማችና የተዋበች ሆናለች የሚሉት አቶ ተሾመ፣ ይህንንም ዓለም እየመሰከረ ነው፡፡ ከተዋቡት የከተማዋ ስፍራዎች አንዱ ደግሞ የመስቀል አደባባይ ነው፡፡ ይህ አደባባይ ከበፊቱ በተለየ ማራኪ ውበትና ምቾትን ተጎናፅፏል፡፡
ይህም የበዓሉ ታዳሚዎች ያለምንም መጨናነቅ የሚያከብሩበትን ዕድል ፈጥሯል፡፡ ቱሪስቶችም ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎችና ዓለማት ወደ ከተማዋ ሲመጡ ከመቼውም ጊዜ በላይ በየቀኑ በአስደማሚ ለውጥ ውስጥ ባለችው ከተማ ዘና እያሉ ደስታቸውን እንዲያጣጥሙ ምቹ አጋጣሚን የሚፈጥር በዓል እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
መስቀል በዩኔስኮ የተመዘገበ መሆኑ፣ አዲስ አበባ ደግሞ በኮሪደር ልማት መዋቧ እና እንደ ከተማም ሆነ እንደ ሀገር ልዩ ልዩ የቱሪስት መዳረሻዎች በመገንባታቸው የጎብኝዎች ቁጥር ይጨምራል፤ የሀገርን ገፅታ የበለጠ ለመገንባት ያግዛል፤ በቱሪዝም ኢኮኖሚው ላይም ትልቅ አቅምን ይፈጥራል ብለዋል፡፡
እንደ አቶ ተሾመ ማብራሪያ የመስቀል በዓል ከአዲስ አበባ ውብ የኮሪደር ገፅታ ጋር የሚፈጥራው ድባብ ቱሪስቶች የቆይታ ጊዜያቸውን እንዲያራዝሙ፣ እንደ አንድነት ፓርክ፣ ብሔራዊ ቤተ መንግስት፣ የዐድዋ ድል መታሰቢያ፣ ሳይንስ ሙዚየምን እና እንጦጦ ፓርክን የመሳሰሉ ስፍራዎችን እንዲጎበኙ ዕድል ይፈጥራል፡፡
የመስቀል ደመራ በዓል ከኮሪደር ልማቱ ጋር የሚፈጥረውን ውብ እና አይረሴ ድባብ በአግባቡ መጠቀም ይገባል የሚሉት አቶ ተሾመ፣ ይህ ደግሞ በአንድ አካል ብቻ ሳይሆን ሁሉም እንደ ኃላፊነቱ የሚተገብረው ነው ብለዋል፡፡
በቱሪዝሙ ዘርፍ ከሚጠበቁ ተግባራት መካከልም በመንግሥት የሚከናወን መሰረተ ልማት የማሟላት ሥራ፣ የግል ባለሀብቱና መሰል አገልግሎት ሰጪ አካላት እንዲሁም በግልና በመንግስት የሚከናወኑ የማስተዋወቅና መሰል ስራዎች አሉ፡፡
ይህንንም ተከትሎ መንግሥት ከሞላ ጎደል በተለይ እንደ አዲስ አበባ መሰረተ ልማቱን አሟልቷል፡፡ በመሆኑም አሁን በትኩረት መስራት ያለብን የአገልግሎት አሰጣጥና ጥራትን ማሻሻል፣ በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብና ከገንዘብ ባሻገር ያለውን የሀገር ገፅታ ግንባታን ማስቀደም፣ ዓለም በተምሳሌትነት የሚጠቅሰውን እንግዳ ተቀባይነታችንን የበለጠ አጉልቶ ማሳየት፣ በየአካባቢው ያለ ዜጋ ቱሪስቶችን ማገዝ፣ መንገድ መምራት እና በቂ መረጃ በመስጠት ሌሎች ቦታዎችንም እንዲጎበኙ በማነሳሳት ዕድሉን በሚገባ መጠቀም አለብን ብለዋል አቶ ተሾመ ተክሉ፡፡
ልክ እንደ ህብረ ብሔራዊነታችን ከተለያዩ ስፍራዎች የተሰባሰቡ ችቦዎች፣ በአደይ፣ በአሽክት እና በቄጤማ ደምቀው በሰፊው ሜዳ ላይ ትልቅ ደመራን ይፈጥራሉ፡፡ በዚህ ወቅት መስቀል አደባባይ መሸት ሲል ደመራው ሲለኮስ ከፍ ብሎ ከሚታየው የብርሃኑ ፀዳል ጋር በኮሪደር ልማቱ እንደ አዲስ የተወለደችውን ከተማ መመልከት ልብን በሀሴት ያረሰርሳል፡፡
በመለሰ ተሰጋ