ኪነ ጥበባዊ መሰናዶዎች በመዲናዋ 

You are currently viewing ኪነ ጥበባዊ መሰናዶዎች በመዲናዋ 

ባለፉት ቀናት የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች እና አዳዲስ ኪነ ጥበባዊ ስራዎች በመዲናዋ አዲስ አበባ  ለጥበብ አፍቃሪያን ሲደርሱ ቆይተዋል፡፡ ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናትም የተለያዩ ጥበባዊ መሰናዶዎች ይደረጋሉ፡፡  ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናት ከተሰናዱ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች መካከል የሥዕል አውደ ርዕይ፣ የአዳዲስ መጻሕፍት ህትመት፣ የቴአትር መርኃ ግብር እና ሌሎች መሰናዶዎች ይገኙበታል፡፡ ለመረጃ ይሆንዎት ዘንድ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል እንደሚከተለው አዘጋጅቷቸዋል፡፡ 

መጻሕፍት

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ገበያ ላይ ጠፍተው የነበሩ አዳዲስ መጻሕፍት ለህትመት አብቅቷል፡፡ ለተደራስያን ከቀረቡ ነባር መጽሐፎች መካከል የራስ ሥዩም መንገሻ ‘የትውልድ አደራ’ እና የፕ/ር ሽብሩ ተድላ ‘የሕያው ፈለግ’ የተሰኙ መጽሐፎች ይገኙበታል። እንዲሁም የኢትዮጵያ ዳር ድንበር፣ ከደስታ ባለፈ ተፈጥሯዊ የሩካቤ ሂደትና ውጤቱ፣ ዝግመተ ለውጥ፣ አካባቢ እና ጤና በኢትዮጵያ፣ የተውኔት ዝግጅት መሠረታውያን፣ መንግሥትና ሀብት እና ታላቁ የግብርና ምርምር ሥርዓት መሪ የተሰኙ መጽሐፎች ታትመው ገበያ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ መጽሐፎቹ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጻሕፍት ማዕከል (ቡክ ሴንተር)፣ በጃፋር የመጻሕፍት መደብር፣ በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ጽህፈት ቤት እና በሌሎችም የመጻሕፍት መደብር የሚገኙ ናቸው፡፡

“የድምጽ እና የቋንቋ ሥርዓት” የተሰኘ አዲስ መጽሐፍ ለንባብ በቃ፡፡ በመምህር ምጽላል ድንግል ሙሉነህ የተጻፈው “የድምጽ እና የቋንቋ ሥርዓት” በቋንቋ ሥርዓትና ተያያዥ ቋንቋ ነክ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፉ በተለያዩ የመጻሕፍት መሸጫ መደብር ውስጥ ይገኛል ተብሏል፡፡

የታዋቂዋ ተዋናይት ሜሮን ጌትነት ‘ሌላ እውነት የለኝም’ የግጥም መድብል መጽሐፍ ለንባብ በቃ፡፡ በተለያዩ ፊልሞችና የቴሌቪዥን ተከታታይ ድራማዎች የምትታወቀው ሜሮን ጌትነት አሁን ደግሞ በአዲስ የግጥም መጽሐፍ እንደገና ተመልሳለች፡፡ መጽሐፉ በተለያዩ የመጻሕፍት መደብሮች ውስጥ ይገኛል፡፡

ሥዕል

“የተመለሱ እይታዎች” አውደ ርዕይ ተከፈተ፡፡ የሠዓሊ ኪሩቤል ተፈሪ የሥዕል ስራዎች የቀረቡበት “የተመለሱ እይታዎች” የተሰኘ የሥዕል አውደ ርዕይ
ባለፈው ሳምንት ረዕቡ መስከረም 7 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ፣ ሐያት ሪጀንሲ ሆቴል ውስጥ በሚገኘው ፈንድቃ የባህል ማዕከል ውስጥ ለእይታ በቅቷል። የሰዓሊው የተለያዩ ጥበባዊ የፈጠራ ሥራዎች የቀረበበት የሥዕል አወደ ርዕዩ እስከ መጪው ጥቅምት 3 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ይቆያል ተብሏል::

ቴአትር

በመዲናችን አዲስ አበባ ቅዳሜ እና እሁድ የተለያዩ ቴአትሮች ይታያሉ፡፡ 12ቱ እንግዶች የተሰኘው ቴአትር ቅዳሜ 8:30 ሰዓት በብሔራዊ ቴአትር ቤት ይታያል። 11፡30 ሰዓት ደግሞ ባሎችና ሚስቶች  የተሰኘው ቴአትር በዚያው በብሔራዊ ቴአትር ይታያል፡፡ እሁድ በ8፡30 ሰዓት ደግሞ ንጉሥ አርማህ ቴአትር፣ እንዲሁም  እምዬ ብረቷ የተሰኘው ቴአትር ደግሞ በዚሁ በብሔራዊ ቴአትር 11፡30 ሰዓት ላይ ይታያል።

በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ደግሞ እሁድ በ8:00 ሰዓት የደመና ዳንኪረኞች የተሰኘው ቴአትር ይታያል፡፡ በተጨማሪም በቀጣይ ቀናት በብሔራዊ ቴአትር የሚታዩት ማክሰኞ በ11፡30 ሰዓት ሦስቱ አይጦች፣ ረዕቡ በ11፡30 ሰዓት የቅርብ ሩቅ ቴአትር፣ ሐሙስ ቀን 11:30 ሰዓት ሸምጋይ ቴአትር፣ አርብ በ11፡30 ሰዓት የሕይወት ታሪክ በብሔራዊ ቴአትር  ለጥበብ አፍቃሪያን ለዕይታ ይቀርባሉ፡፡

በአብርሃም ገብሬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review