ቤታቸው የታደሰላቸው ወ/ሮ ዝናሽ ቸኮል
የ75 ዓመቷ አረጋዊት ወ/ሮ ዝናሽ ቸኮል የ2018 አዲስ ዓመትን በታደሰ ቤት ከተቀበሉት መካከል ናቸው፡፡ ታድሶ አዲስ ውበት፣ አዲስ ገፅታ፣ አዲስ መንፈስ በፈጠረባቸው ቤታቸው በገቡበት ወቅት ተገኝተን ደስታቸውን ተጋራን፡፡
እኚህ አረጋዊት በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 በተለምዶ ግንፍሌ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ለሠላሳ ሦስት ዓመታት ኖረዋል፡፡ ከሦስት አስርት ዓመታት በተሻገረ ዕድሜ በኖሩበት በዚህ አካባቢ በርካታ ውጣ ውረዶችን ማስተናገዳቸውን አልሸሸጉም፡፡
“ህይወት መልኳን ያዞረችብኝ ባለቤቴን በሞት ባጣሁበት ሰዓት ነበር። የሞላ እና የሞቀ ትዳር ውስጥ እኖር ነበር፡፡ ይህ አስከፊ አጋጣሚ ከተከሰተ ሃያ አምስት ዓመት አልፎታል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ምንም የተረጋጋ ሕይወት አልነበረኝም፡፡ አራስ ልጄን በአንድ እጄ ይዤ ጡት ሳጠባ፣ በሌላኛው እጄ ደግሞ እንባዬን እያበስኩ ነበር ኑሮዬን ስገፋ የቆየሁት፡፡ ʻበእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍʼ እንደሚባለው፤ የክረምቱ ዝናብ፣ የበጋው ፀሐይ የተፈራረቀባት ደሳሳዋ ጎጆዬ በላዬ ላይ መፍረስ ጀምራ ነበር፡፡” በማለት ያለፉበትን አስከፊ ጊዜ ይተርካሉ፡፡
ባለቤታቸውን ካጡ በኋላ፣ አራስ ልጃቸውን ብቻቸውን ሰው ቤት ልብስ በማጠብ፣ እንጀራ በመጋገር እንዲሁም ደግሞ አሻሮ በመቁላት ያሳደጉት እኝህ አረጋዊት፤ የደሳሳ ቤት ኑሮአቸውን አስከፊ ያደረገባቸው ዝናብና ሐሩሩ ብቻ አልነበረም፡፡ የተለያዩ ነፍሳት እንዲሁም አይጦች እንዳሻቸው ገብተው የሚወጡበት ቀዳዳ በመብዛቱ፣ እረፍት አልባ ሌሊቶችን እንዲያሳልፉ ምክንያት ሆኗቸዋል፡፡
“የህዳሴ ግድባችን ከዳር ደርሶ መላ ኢትዮጵያውያንን እንዳስደሰተው ሁሉ፤ የእኔም ቤት ቀን ወጥቶለት አምሮ እንደ አዲስ ተሞሽሯል፡፡ በአዲሱ ቤቴ ውስጥ አዲስ ሶፋ፣ ወንበሮች፣ ጠረጴዛ እና አልጋ ተሟልቶልኛል፡፡ ዓመትንም በአዲስ መንፈስ ተቀብያለሁ፡፡ ያለው ለሌለው ሲረዳ ጎዶሏችን ይሸፈናል” ሲሉ የተሰማቸውን ደስታ እንባ በተቀላቀለ ሁኔታ ገልፀዋል፡፡
በክረምቱ ወቅት እንደወይዘሮ ዝናሽ ቸኮል ላሉ በቁጥር 13 ለሚሆኑ የአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 አስተዳደር አቅመ ደካማና አረጋዊያን ነዋሪዎች ቤታቸው ታድሶላቸዋል፡፡ ይህንን ሥራ አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡት በወረዳው የህብረተሰብ ተሳትፎ እና በጎ ፍቃድ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ገረመው አዝመራው በአስተያየታቸው፤ “በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት የበርካቶችን የአቅመ ደካሞች ቤት በማደስ፣ የትራፊክ አገልግሎት በመስጠት፣ የሰላም ዘብ በመሆን፣ የደም ልገሳ፣ የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት እና መሰል አገልግሎቶችን በጎ ፍቃደኞችን በማሳተፍ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ የአቅመ ደካሞችን ቤት እድሳት ለማድረግ በወረዳው ውስጥ የከፋ ችግር ያለባቸውን እንደየክብደቱ ቅድሚያ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡” ብለዋል፡፡
ነዋሪነታቸውን በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 በተለምዶ አበበ ቢቂላ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ያደረጉት አቶ አንተነህ ተስፋዬ፤ ባሳለፍነው ጷጉሜን ላይ ነበር አዲስ ቤታቸውን ተረክበው አዲስ ዓመትን የተቀበሉት፡፡ ከስምንት ዓመት በፊት በደረሰባቸው የመኪና አደጋ ህልማቸው ጨልሞ፤ በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ሆነው ቀናትን፣ ወራትንና ዓመታትን በመቁጠር ላይ ሳሉ ነበር የበጎ ፈቃደኝነት በጎ ተግባር የደረሰላቸው፡፡
ወድቆ መነሳት ያለ መሆኑን በማመን ጎጇቸውን ለማቅናት አቅማቸው የፈቀደውን ስራ ብቻ በመከውን የእለት ጉርሳቸውን ለማሟላት ጥረት ቢያደርጉም፣ ህልማቸውና አኗኗራቸው ሊጣጣም ያልቻለው አቶ አንተነህ፤ ከእርሳቸው አልፎ በቤተሰቦቻቸው ላይ ተፅዕኖ መፈጠሩ አልቀረም፡፡ ሁለቱን ልጆቻቸውን ለማስተማር ችግር ገጥሟቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። የኑሮ ውጣ ውረድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጫናቸው ሲመጣ፤ በእርጅና ምክንያት እየተጎሳቆለ የመጣውን መኖሪያ ቤታቸውን ማደስ አልቻሉም። ጎርፍ ለሚያስገባው መኖሪያቸው መላ ለማበጀት ተቸግረው ባሉበት ወቅት ለመፍትሄ በራቸውን ያንኳኳው የበጎ ፍቃደኞች በጎ እጅ እንደማለዳ ፀሐይ ቀሪ ዘመናቸውን ሊያበራ እንደመጣ ተዓምር ይመስሉታል፡፡
እንደ አቶ አንተነህ ገለፃ፤ በክረምት ወራት የሚዘንበው ዝናብ የቤታቸውን መሰረት ከማዛባት ባሻገር እርጥበቱ የኤሌክትሪክ አደጋ መፈጠር ምክንያት ጭምር ሆኗል፡፡ በተለይ ካለማቋረጥ አምፖሉ ብልጭ ብልጭ ሲል ከአሁን አሁን እኔና ቤተሰቤ አለቅን በማለት የሰቆቃ ህይወትን እንመራ ነበር፡፡ ባለሁለት ክፍል ቤታቸው በተዋበ በርና መስኮት ስርዓቱን በጠበቀ አግባብ ተሰትሮ ሲያዩት በደስታ እንዳነቡ ገልፀዋል፡፡ በተለይ እነዚያ ለመውጣትና ለመግባት አስቸጋሪ የነበሩ በሮች ከማዘንበላቸው ባለፈ ከዛሬ ነገ ይወድቁ ይሆን ብለው ይሰጉ ነበር፡፡ አሁን ግን ቀኑን ቀን፤ ሌሊቱን ሌሊት አስመስሎ ድምቀትን የቸራቸው መኖሪያ ቤታቸው ትልቅ የህይወት ተስፋን እንዲያገኙ አግዟቸዋል፡፡
“በተስፋ መኖር እድሜ እንዲቀጥል ያደርጋል” የሚሉት አቶ አንተነህ፤ “ቀድሞ በነበረው ቤት ውስጥ አይደለም ብሩህ ተስፋን ይቅርና ለደቂቃ እንኳን ቤት ውስጥ ሳሳልፍ ድባቴ እና ጭንቀት ነበር የሚሰማኝ፡፡ አሁን ግር ብሩህና የማያቋርጥ ሰላም ባለበት ቤት ውስጥ በመገኘቴ ቀጣዩ የህይወት ዘመኔ የተሻለ እንዲሆን ያደርገኛል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሠው ተኮር የልማት መርሃ ግብርን እያከናወነ ያለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፤ ዘመናዊና ምቹ የመኖሪያ ቤቶችን ለነዋሪዎች የማቅረቡን ሥራ አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በቅርቡም ከተማ አስተዳደሩ በሺዎች ለሚቆጠሩ ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት አስተላልፏል፡፡ ይህንን በተመለከተ በማህበራዊ የትስስር ገፃቸው ላይ ሃሳባቸውን ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፤ “በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ያስገነባናቸውን 1 ሺህ 671 ያህል ቤቶች ለሀገር ባለውለታዎች፣ ለአረጋውያን፣ ለአካል ጉዳተኞች፣ ለከፋ ማህበራዊ ችግር ለተጋለጡ፣ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ እና በወንዝ ዳርቻዎች ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች አስረክበናል” ብለዋል፡፡ አያይዘውም፤ በዚህ ተግባር ውስጥ ካላቸው ያለ ስስት ሰጥተው ከከተማ አስተዳደሩ ጎን ለነበሩ ባለሀብቶች ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወይዘሮ አስራት ንጉሴ ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት ማብራሪያ፣ የክረምቱ መርሃ ግብር እስከ መስከረም 30 ድረስ ይቀጥላል፡፡ በ15 ዋና ዋና መርሃ ግብሮች እና 19 ንዑሳን መርሃ ግብሮችን በመያዝ ነበር ወደ ተግባር የተገባው፡፡ የቤት እድሳትን በተመለከተ በክረምቱ መርሃ ግብር 2 ሺህ 500 መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት የታቀደ ሲሆን ወደ 3 ሺህ 154 የሚሆኑትን ገንብቶ ማጠናቀቅ ተችሏል፡፡ ቁጥራቸው ከ500 ሺህ በላይ ለሚሆኑት ማዕድ ለማጋራት ታቅዶ ከ600 ሺህ በላይ ለሚሆኑት ማጋራት ስለመቻሉ ገልፀዋል፡፡
ነፃ ህክምናን በተመለከተ እንዲሁ ቁጥራቸው ከ125 ሺህ በላይ ዜጎችን ተደራሽ ለማድረግ ታቅዶ 207 ሺህ በላይ የሚሆኑትን መድረስ ተችሏል፡፡ ይህ ሁሉ ሊሰራ የቻለው የመንግስት ብሎም የግል የህክምና ተቋማትን በማሳተፍ ጭምር ነው፡፡ በደም ልገሳ መርሃ ግብር እንዲሁ 40 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ታቅዶ ከ41 ሺህ ዩኒት በላይ ደም ከበጎ ፍቃደኞች እንዲሁም ከከተማዋ ነዋሪዎች ለመሰብሰብ ተችሏል፡፡ ቁጥራቸው 65 ሺህ የሚሆኑ ተማሪዎችን በክረምት መርሃ ግብር የማጠናከሪያ ትምህርት ለመስጠት ታቅዶ ለ68 ሺህ 107 ለሚሆኑ ተማሪዎች በበጎ ፍቃደኛ መምህራን ትምህርቱ ተሰጥቷል፡፡ ሌሎችም አገልግሎቶች ከእቅድ በላይ ለማሳካት ስለመቻሉ ተናግረዋል፡፡
እንደ ምክትል ኮሚሽነሯ ገለጻ፣ በክረምቱ መርሃ ግብር እስከ መስከረም 6 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ቁጥራቸው ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ በጎ ፍቃደኞች በድግግሞሽ በሁሉም መርሃ ግብሮች ላይ ተሳትፈዋል፡፡ የከተማዋን እድገትና ልማት በማፋጠን የነዋሪውን ኢኮኖሚያዊ እና ማህባራዊ ችግሮች ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ውሰጥ በጎ ፍቃደኞች የቀኝ እጅ ስለመሆናቸው ወ/ሮ አስራት የገለፁ ሲሆን በተሰራው ስራ 5 ነጥብ 9 ቢሊየን በላይ የመንግስት ወጪን ለማዳን ተችሏል፡፡
በበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሚከወኑ ተግባራት የማህበረሰባችንን የመረዳዳትና የእርስ በእርስ ግንኙነታችንን አጠናክሯል። አቅመ ደካሞች፣ አረጋውያንና አካል ጉዳተኞች ማህበራዊ ተሳትፏቸውና ተጠቃሚነታቸው ማሳደግ፣ በጥሩ ስብዕና የታነፁ ወጣቶችን ማፍራት ተችሏል። በመንግስት ይሸፈን የነበረውን ወጪ በማዳን ወደ ሌሎች ልማታዊ አጀንዳዎች ማስፈጸሚያነት እንዲውል አስቻይ ሁኔታዎች ስለመመቻቸቱ ጭምር ምክትል ኮሚሽነሯ አስረድተዋል፡፡
በሄለን ጥላሁን