የለውጡ መንግሥት ኪነ ጥበብን የኢትዮጵያ ብልፅግና ማሳለጫ አድርጎ እንደሚመለከት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የህጻናትና ወጣቶች ቴአትር ኮምፕሌክስን መርቀዋል።
በመድረኩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኪነ ጥበብ የእሴት መፍጠሪያ፣ የስልጣኔ ማስፈንጠሪያ እና የትርክት መቀየሪያ መሳሪያ ነው።
ይህንን መሳሪያ በዓላማ መምራትና መደገፍ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የለውጡ መንግሥት ኪነ ጥበብን የሚመለከተው የኢትዮጵያ ብልጽግና ማሳለጫ አድርጎ መሆኑን ጠቅሰው፤ መንግሥት ለኪነ ጥበብ ትልቅ ቦታ በመስጠት አያሌ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑንም አስታውቀዋል።
የህፃናትና ወጣቶች ቴአትር ማዕከል መገንባቱ መንግሥት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት የሚያሳይ መሆኑንም አንስተዋል።
ኪነ ጥበብ የወል ትርክትን በመፍጠር ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በመገንባትና በማስረጽ ረገድ የማይተካ ሚና እንዳለው የለውጡ መንግስት እንደሚያምን ተናግረዋል።
ይህንን ሚናውን መወጣት እንዲችል ከመንግስት እና ከያንያን የሚጠበቁ ነገሮች መኖራቸውን አንስተው፤ ፖሊሲ፣ የህግ ማዕቀፍ እና ማበረታቻ ከመንግስት የሚጠበቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ኪነ ጥበብን ለሀገር ግንባታ በሚጠቅም መልኩ መፍጠርና ማሳደግ ደግሞ ከከያኒያን የሚጠበቅ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ መጠቀም እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ መንግስት ባለፉት ሰባት ዓመታት በተቋማት ግንባታ ሂደት ለኪነ ጥበብ ትልቅ ቦታ መስጠቱን ገልጸዋል።
በኪነ ጥበብ ዘርፍ ከከያኒው በተጫማሪ የኪነ ጥበብ ምሁራንም በእውቀት መሳተፍ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ኪነ ጥበብን በዒላማ ሳይሆን በዓላማ መምራት እንደሚገባ ገልጸው፤ ለዚህም መንግስት የሚጠበቅበትን እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።
አዲስ አበባ ለኪነ ጥበብ ምቹ እየሆነች መምጣቷን ጠቅሰው፤ በበርካታ አካባቢዎች አምፊ ቴአትርና ፕላዛዎች እየተገነቡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
እነዚህ የኪነ ጥበብ ሥፍራዎች የአብርሆትና የሀገር ዕድገት ጥበብን እንደሚሹ ገልጸው፤ ከተማዋ በኪነ ጥበብ መድመቅ እንዳለባትም አመልክተዋል።
በአሁኑ ወቅት የተገነቡ የኪነ ጥበብ ማዕከላት ጥቅም ላይ እንዲወሉ የከተማ አስተዳደሩና ተቋማት ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
ኪነ ጥበብን በማጎልበት ኢትዮጵያን በጋራ እንገንባ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።