ምሽት ንግድ በ4 ኪሎ

You are currently viewing ምሽት ንግድ በ4 ኪሎ

• በአራዳ ክፍለ ከተማ በመንገድ ዳር ከሚገኙ የንግድ ተቋማት 873 የሚሆኑት በምሽትም እንደሚነግዱ ተገልጿል

በሰለጠነው ዓለም በማታው ክፍለ ጊዜ የጦፈ የንግድ እንቅስቃሴ እንደሚደረግ መረጃዎች ያመላክታሉ። ኤ.ቢ.ሲ ኒውስ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2024 (24 ሃወርስ ትራዲንግ ሲቲስ) በሚል ርዕስ ባወጣው መረጃ በተለይ በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በእስያ እና በአንዳንድ የአረቡ ዓለም ሀገራት የምሽት ንግዶች ይዘወተራሉ። በዚህም በዓመት ውስጥ ከ200 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት ሀብት ይንቀሳቀሳል።

እንዲህ ያለው ባህል በኢትዮጵያም መዘውተር ጀምሯል። በተለይ የኮሪደር ልማት ስራን ተከትሎ በዚህ ረገድ መልካም የሚባል አዝማሚያ ተፈጥሯል። የአዲስ አበባ ከተማ ደግሞ ድርጊቱን በህግ ማዕቀፍም ጭምር አስደግፋ ወደማስተግበር ከገባች ሰነባብታለች። ለመሆኑ በአራዳ ክፍለ ከተማ የዚህ ደንብ ትግበራ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል? ምን ያህሎችስ እየተጠቀሙበት ነው? የሚል ፍተሻ አድርገናል።

የኮሪደር ልማት በተከናወነባቸው የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ዋና መንገዶች ዳር የሚገኙ የንግድ ተቋማት እስከ ምሽት ሶስት ሰዓት ተኩል ድረስ እንዲሰሩ የሚያደርግ የምሽት ንግድ ተቋማትና ትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ደንብ ቁጥር 185/2017 የካቲት 29 ቀን 2017 ዓ.ም ጸድቆ ወደ ትግበራ መግባቱ ይታወሳል፡፡ ተቋማቱ እስከ ምሽት ቆይተው ህዝቡን እንዲያገለግሉ መደረጉ ለነጋዴዎች ተጨማሪ ገቢ የሚፈጥር ከመሆኑም በላይ በተለያዩ ምክንያቶች በቀኑ ክፍለ ጊዜ መሸመት የማይችለውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርግ እንደሆነ ይታመናል፡፡

የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል የምሽት የንግድ እንቅስቃሴ ያለበትን ደረጃ ለመታዘብ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ተንቀሳቅሶ ቅኝት አድርጓል፡፡ አራት ኪሎ አካባቢ አንዱ የቅኝታችን አካል ሲሆን፣ አደባባዩን ተከትሎ መሬት ውስጥ በተሰራው መተላለፊያ ዙሪያ ያሉ በርካታ ሱቆች በምሽት የሞቀ የንግድ እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉ ማወቅ ችለናል፡፡

በአራት ኪሎ አደባባይ ዙሪያ በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ ወጣቶች የምሽት ንግዱ ተጨማሪ ገቢ የማግኘት ዕድል እንደፈጠረላቸው ነግረውናል፡፡ በአራዳ ክፍለ ከተማ አራት ኪሎ ፕላዛ ስር በኮስሞቲክስ ንግድ ስራ የተሰማራችው ወጣት ሴና ገብሬ፣ የምሽት ንግድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሞቀ መምጣቱንና መልካም የሚባል ገቢ እንደሚገኝበት ነው የተናገረችው፡፡

አካባቢው የ24 ሰዓት ጥበቃ ያለው በመሆኑ አምሽቶ ለመስራት ከፀጥታ አንፃር ምንም የሚያሰጋ ነገር እንደሌለ የምትጠቅሰው ወጣቷ፣ አልፎ አልፎ የትራንስፖርት ችግር ከማጋጠሙ በስተቀር ስራው ምቹና አትራፊ መሆኑን ገልፃለች፡፡

በአዲስ ፋና ጠቅላላ ሸቀጣሸቀጥና ሆቴሎች ንግድ አክሲዮን ማህበር የሽያጭ ሰራተኛ የሆኑት ወይዘሮ ፍሬህይወት ደበበ የተባሉ አስተያየት ሰጪም በኮሪደር ልማት በለሙ አካባቢዎች ያሉ የንግድ ተቋማት እስከ ምሽቱ 3፡30 አገልግሎት መስጠታቸው ለከተማዋም ሆነ በዘርፉ ለተሰማሩ አካላት ተጨማሪ ገቢ የሚፈጥር እንደሆነ ገልፀው፣ ሆኖም ግን የህብረተሰቡ የምሽት ግብይት ልማድ አናሳ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በምሽት የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ አሽከርካሪዎች ከታሪፍ በላይ ማስከፈል፣ በቂ የትራንስፖርት አገልግሎት አለመኖር፣ የመብራት መቆራረጥ እና መሰል ችግሮች በስራው ላይ የተወሰነ ክፍተት እየፈጠሩ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በአራዳ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ‘ቱሪስት ሆቴል’ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ አትክልትና ፍራፍሬ (ጁስ) ቤት ከፍተው እየሰሩ ያሉት ነጋዴ አቶ ሃብተሚካኤል ወልዱም የንግድ ተቋማት እስከ ምሽቱ ሶስት ሰዓት ከሰላሳ አገልግሎት እንዲሰጡ በከተማ አስተዳደሩ ከተወሰነ ጀምሮ የምሽት ንግድ ስራ እየሰሩ እንደሆነ አስታውሰው፣ ይህም ነጋዴዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግና ለከተማዋ እድገትም አጋዥ መሆኑን ነው ያስረዱት።

በአራዳ ክፍለ ከተማ ንግድ ፅህፈት ቤት የንግድ ኢንስፔክሽንና ሬጉላቶሪ ቡድን መሪ አቶ ገለታው ለገሰ፣ በክፍለ ከተማው ካሉ 8 ወረዳዎች በ6ቱ የኮሪደር ልማት ስራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰው፣ የኮሪደር ልማት በተካሄደባቸው አካባቢዎች በመንገድ ዳር ካሉ የንግድ ተቋማት 873 የሚሆኑ ተቋማት የምሽት ንግድ እየሰሩ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

እነዚህ ድርጅቶች የስራ ባህላቸውን እንዲያሻሽሉ በተደጋጋሚ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎች ሲሰሩ ከመቆየታቸውም ሌላ የከተማ አስተዳደሩም እስከ ምሽቱ ሶስት ሰዓት ከሠላሳ ድረስ እንዲሰሩ ደንብ ማውጣቱን ያስታወሱት አቶ ገለታው፣ ይህን ለማስፈፀምም የክትትልና ቁጥጥር ስርዓት መዘርጋቱን አንስተዋል፡፡

በአብዛኛው ነጋዴ ዘንድ የምሽት ስራ የተለመደ ባለመሆኑ አንዳንዶቹ መደበኛ ስራቸውን ቀን ሰርተው በማታው ክፍለ ጊዜ እንደሚዘጉ ገልፀው፣ ለእነዚህም በር ለበር በመዞር ግንዛቤ መሰጠቱን አስታውቀዋል፡፡

በክፍለ ከተማ ደረጃ በጉዳዩ ላይ ሰፊ ግንዛቤ የተፈጠረ ቢሆንም አንድ ቀን አምሽተው ሰርተው በሌላው ጊዜ ደግሞ የማይሰሩ እንደሚያጋጥሙ ገልፀው፣ ለዚህም የመኖሪያ አካባቢያቸው ከአዲስ አበባ ውጪ እና አዲስ አበባም ሆኖ ዳር ወይም ራቅ ያለ አካባቢ መሆኑን በምክንያትነት ይጠቅሳሉ ብለዋል፡፡

የትራንስፖርት አለመኖርና ከፀጥታ ጋር ተያይዞም እንደ ችግር እንደሚያነሱ የጠቀሱት አቶ ገለታው፣ ጉዳዩን በሚመለከት የወጣው ደንብ ቁጥር 185/2017 የንግድ ስራውንና የትራንስፖርት አገልግሎቱን ሊያሳልጥ የሚችል እንደሆነም አስረድተዋል። የትራንስፖርትና መሰል ችግሮችን ለማቃለል ከሚመለከታቸው መንግስታዊ ተቋማት ጋር እየተሰራ ሲሆን፣ ለችግሩ እልባት ለመስጠት ጥረት እየተደረገ ነውም ብለዋል፡፡   

በምሽት ንግድ ስራ የተሰማሩ ድርጅቶች፣ ሰራተኞችና ባለቤቶች መኖሪያ ቤት ከስራ ቦታቸው ሩቅ ቢሆንም እንኳ ለችግር እንዳይጋለጡ የፀጥታ መዋቅሩ እንደ አዲስ አበባ በየቦታው በትኩረት እየሰራ መሆኑን አውስተው፣ ከተማ አቀፍ ስራ በቅንጅት እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ ገለታው ገለፃ፣ የንግድ ተቋማት በምሽት የስራ እንቅስቃሴያቸው ላይ እንደሚያጋጥማቸው ከሚያነሱት የፀጥታና ትራንስፖርት ችግር፣ የፓርኪንግ አገልግሎት እጥረት በተለይ በኮሪደር የለሙ መንገዶች ዳር ተሽከርካሪ ማቆም አለመቻል ደንበኞች በቀላሉ መጥተው መገበያየት እዳይችሉ አድርጓል፡፡

ታድያ የምሽት ንግድ በሚሰራባቸው አካባቢዎች ተሽከርካሪ በጊዜያዊነት አቁሞ መግዛት የሚቻልበትን አግባብ በማመቻቸት ችግሩን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ በስራ ቦታ እና መኖሪያ አካባቢም የፀጥታ ችግር እንዳያጋጥማቸው በየክፍለ ከተማው ያሉ የሰላም ሰራዊት አባላት፣ የፖሊስ አካላትና ደንብ አስከባሪዎች በቅንጅት እየሰሩ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡

የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በአራዳ ክፍለ ከተማ ተዘዋውሮ ባደረገው ቅኝት ከፒያሳ ወደ አራት ኪሎ፣ ከአራት ኪሎ በስላሴ ወደ ቀበና፣ ከአራት ኪሎ ወደ እንጦጦ ባሉ መስመሮች የተካሄደውን የኮሪደር ልማት ተከትሎ የምሽት የንግድ እንቅስቃሴው የሞቀ መሆኑን ታዝቧል፡፡ በተለይም 4 ኪሎ ፕላዛ እና 4 ኪሎ የገበያ ማዕከል እና የመኪና ማቆያ ለአካባቢው ልዩ ድምቀት ፈጥረዋል፡፡

4 ኪሎ የገበያ ማዕከል እና የመኪና ማቆሚያ ከመሬት በታች የተገነቡ ዘመናዊ 102 የስጦታና የአልባሳት መደብሮች፣ ካፍቴሪያዎች፣ ማንበቢያ ስፍራዎች፣ ሱፐር ማርኬቶችን ያካተተ ነው፡፡ በተጨማሪም ከ100 በላይ ተሽከርካሪዎችን በአንድ ጊዜ ማቆሚያና በአንድ ጊዜ እስከ 5 ሺህ ሰዎችን መሰብሰብ የሚያስችል የፕላዛ፣ የአምፊ ቴአትርና የተለያዩ የጥበብ ስራዎችን ማቅረቢያ ስፍራዎችን ይዟል። በተመሳሳይ 4 ኪሎ ፕላዛም በውስጡ የሀገር ውስጥ አልባሳት፣ መዋቢያዎች፣ ወርቅና ብር መሸጫ ቤቶች፣ የስልክ መሸጫዎች፣ የፈጣን ምግብ አገልግሎት እና መሰል የንግድ አገልግሎቶችን ይሰጣል፡፡ እነዚህ ስፍራዎች ለምሽት ንግድ ስራ ተጨማሪ አቅምና ድምቀት ፈጥረዋል፡፡

በሸዋርካብሽ ቦጋለ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review