መገናኛ ብዙሃን የኢሬቻ በዓል አከባበር ባህላዊ እሴትን በማስተዋወቅና በማስተማር ረገድ ያላቸውን ሚና እንዲወጡ የኦሮሚያ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ሀላፊ ወሮ ጀሚላ ሲንቢሩ ጥሪ አቀረቡ ።
የኦሮሚያ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ የ2018 ዓ.ም የኢሬቻ በአል አከባበር በተመለከተ ከሃገር ውስጥ እና ከውጭ ሃገር የሚድያ ባለሞዎች ጋር በኦሮሞ ባህል ማዕከል ውይይት አካሄዷል፡፡ የዘንድሮ የኢሬቻ በዓል “ኢሬቻ ለሀገር ማንሰራራት ” በሚል መሪ ቃል የሚከበር ሲሆን፣ ይህም በዓሉ ኢትዮጰያ የምትገኝበትን የማንሰራራት ጉዞ የሚገልፅ ነው ሲሉ ሃላፊዋ ገልፀዋል ፡፡
የመገናኛ ብዙሃን በዓሉን ለማስተዋወቅ ላደረጉት አስተዋፅኦ አመስግነው፣ የኢሬቻ በዓልን በተመለከተ የተሳሳተ አመለካከትን የሚያራምዱ አንዳንድ አካላት ወደ ትክክለኛው እሳቤ እንዲመጡ ማስቻል ይገባል ብለዋል። የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሀላፊ አቶ ሀይሉ አዱኛ በበኩላቸው፣ መገናኛ ብዙሀን ትክክለኛውን የኢሬቻ ባህላዊ እሴት በማስተዋወቅ የተሳሳቱ እሳቤዎችን ማረም እንደሚገባቸዉ አስገንዝበዋል።

ኢሬቻ ብሄር ብሄረሰቦችን ጨምሮ ከተለያዩ የዉጭ ሃገራት የሚመጡ ቱሪስቶች የሚታደሙበት በአል በመሆኑ ባህላዊ እሴቱን በጠበቀ መንገድ እንዲከበር መገናኛ ብዙሀን የማስተማር ሚናቸውን እና ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ በአፅንኦት ተናግረዋል።
የኢሬቻ በዓል በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት ዩኔስኮ እንዲመዘገብ መገናኛ ብዙሃን ባህሉን የማስተዋወቅ ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
በሄለን ተስፋዬ