የዓድዋ ድል መታሰቢያ የጥበብ ሥራዎችን ለማስፋት ትልቅ ድርሻ አለው

You are currently viewing የዓድዋ ድል መታሰቢያ የጥበብ ሥራዎችን ለማስፋት ትልቅ ድርሻ አለው

AMN – መስከረም 19/2018 ዓ.ም

የዓድዋ ድል መታሰቢያ የጥበብ ሥራዎችን በስፋት ለማከናወን ትልቅ አስተዋጽዖ እንዳለቅው የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ገለጹ፡፡

በተለያዩ ቋንቋዎች ይዘቶችን በመፍጠር የሚታወቁት የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች በዓድዋ ድል መታሰቢያ የሚገኙ ለኪነ-ጥበብ ዕድገት አስተዋጽዖ እንዲያበረክቱ ታስቦ የተሰሩ ሲኒማ ቤቶች እና አንፊ ቴአትሮችን ጎብኝተዋል፡፡ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ተገንብቶ ከተጠናቀቀ በኋላ በርካታ አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል፡፡

ሙዚየሙ አቅፎ ከያዛቸው ታሪካዊ ቅርሶች ባሻገር ሲኒማ ቤቶች እና አንፊ ቴያትር ቤቶችም የሚገኙበት ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ የቤት ውስጥ ስፖርታዊ ጨዋታዎች የሚካሄዱባቸው ሥፍራዎችንም ያካተተ ነው ፡፡ በርከት ያሉ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች በዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም የሚገኙትን ድል እና ጋሻ የተሰኙትን ሁለት ሲኒማ ቤቶች ጨምሮ የተለያዩ ታሪክ ዘካሪ ቅርሶችን ጎብኝተዋል፡፡

ሃኒያ አሊ (ሃኒያ አሊ ኒውስ) በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ዜናዎችን ነው የምትሰራው፤ በጉብኝቱ ብዙ የማታውቃቸውን ነገሮች እንዳየች በጉብኝቱ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራት ቆይታ ተናገራለች፡፡ ከዚህ ቀደም አርቲስቶችም ሆኑ ቲክ ቶከሮች የተለየ ቦታ ሲፈልጉ ሌሎች ሀገሮች መሄድን ይመርጡ እንደነበር ያነሳችው ሃኒያ፣ አሁን ላይ ግን ሀገራቸው ምቹ መሆኗን ገልፃለች፡፡

በአዳራሽ ውስጥ እና ከአዳራሽ ውጭ ለሚሰሩ የተለያዩ ሥራዎች የተመቻቸ ሁኔታ መፈጠሩም እንዳስደሰታት ተናግራለች ፡፡ ሄዋን ድረስ እና ሄርሜላ ፍቃዱ፣ የይዘት ስራዎችን በጋራ ነው የሚሰሩት በአድዋ ድል መታሰቢያ በተመለከቱት ነገር መደነቃቸውን ገልጸዋል፡፡

እንደ ሀገር የጥበብ ሥራዎችን በስፋት ለማከናወን በቂ ሥፍራዎች እንዳልነበሩ ያነሱት ቲክቶከሮቹ፣ በዚህ ቦታ እነዚህ ሥፍራዎች ለአገልግሎት ክፍት መሆናቸው የጥበብ ሥራዎችን ለማስፋት ጥሩ አጋጣሚ እንደሚፈጥሩ አመላክተዋል፡፡ (አደመ እና ቤተሰቡ) በሚል የቲክ ቶክ ገጹ የሚታወቀው አደመ እንዳሻው፣ እንደ ሀገር የተሰሩት የሲኒማ፣ የቴአትር እና አንፊ ቴአትር መድረኮች ለመጪው ትውልድ ትልቅ ተስፋዎች መሆናቸውን ገልጿል፡፡

የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎቹ የኢትዮጵያውያን መገለጫ፣ የመላው ጥቁር ህዝቦች ኩራትና ድል የሆነውን የአድዋ ድል መታሰቢያን ለሀገራቸው ብሎም ለዓለም ለማስተዋወቅም ቃል ገብተዋል፡፡

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review