የመደመር መንግሥት መጽሐፍ ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት በቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ተካሄደ

You are currently viewing የመደመር መንግሥት መጽሐፍ ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት በቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ተካሄደ
  • Post category:ፖለቲካ

AMN – መስከረም 19/2018 ዓ.ም

በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጻፈውና በቅርቡ ተመርቆ ለንባብ የበቃው የመደመር መንግሥት መጽሐፍ በቦሌ ክፍለ ከተማ ከሁሉም ወረዳዎች የተውጣጡ የሕብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ የፓናል ውይይት ተደርጎበታል።

የመደመር መጽሐፍ ከዚህ ቀደም፤ መደመር፣ የመደመር መንገድ እንደዚሁም የመደመር ትውልድ በሚሉ ሶስት ርዕሶች መታተሙ የሚታወስ ሲሆን፤ ይህኛው የመደመር መንግሥት መጽሐፍ አራተኛው ነው። የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ እሸቱ ለማ (ዶ/ር) ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፤ ከመጽሐፉ ሁለት ነገሮችን እንረዳለን ብለዋል።

እነርሱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሀገሪቱን ስብራት ለመጠገን ያላቸውን ቁርጠኝነት እና ከመጻህፍቱ ሽያጭ የሚገኘውን ገቢ ለትውልድ ቀረጻ እና ለሀገር ግንባታ እንዲውል መወሰናቸው መሆኑን አንስተዋል።

ሀገራችን ከከፍታ ላይ እንዳትደርስ ያደረጋት የአስተሳሰብ ስብራት በመኖሩ መሆኑን መጽሐፉ መነሻ እንደሚያደርግ የተናገሩት ዶ/ር እሸቱ፤ ከሃሳብ ባሻገር መሬት ላይ የሚታይ የልማት፣ የሠላምና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እውን እየሆነ ነው ብለዋል።

የፓናል ውይይቱን የመሩት የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ሚኤሳ ኤለማ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ እያንሰራራች መሆኑን ጠቅሰው ይህንን ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር የሃሳብ ልዕልና መከበር ይኖርበታል ብለዋል።

በዓለም ላይ አለመግባባቶች ግጭቶችና ሰላም ማጣት እየተስፋፋ የመጣው የሃሳብ ስብራት በመኖሩ ነው ብለዋል። ሃላፊው ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና ከፍታ እንድታመራ የሀሳብ ልዕልናን ማረጋገጥ ይኖርብናልም ነው ያሉት።

ለሀገር በቀል ህመም ሀገር በቀል መድሃኒት በእጅጉ ያስፈልጋል ያሉት ሃላፊው፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የተጻፈው የመደመር መጽሐፍ ለሀገር በቀል ችግር ሀገር በቀል መፍትሄን የሚያመላክት ነው ብለዋል።

የመደመር መንግስት መጽሐፍ እና አንድምታው ላይ ጥልቅ ሙያዊ ትንታኔ በዕለቱ ፓናሊስቶች የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ሙሉጌታ አየለ (ዶ/ር) እንዲሁም በተመራማሪ ታምሩ ፈይሳ (ዶ/ር) አማካኝነት ተካሄዷል።

በውይይቱ ላይ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎችና ሀደ ሲንቄዎችም ጭምር ተሳትፈዋል።

በምትኩ ተሾመ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review