ሰው ሰራሽ አስተውሎት ተጽዕኖ የሚያሳድርባቸው የስራ ዘርፎች

You are currently viewing ሰው ሰራሽ አስተውሎት ተጽዕኖ የሚያሳድርባቸው የስራ ዘርፎች

AMN – መስከረም 19/2018 ዓ.ም

ሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) በአሁኑ ወቅት በአዎንታዊ እና በአሉታዊ መንገድ በሰው ልጆች የዕለት ተዕለት ህይወት ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ይገኛል።

ሰው ሰራሽ አስተውሎት ኮምፒውተሮች የተለያዩ የተሻሻሉ ተግባራትን እንዲያከናውኑ የሚያስችል የቴክኖሎጂ ስብስብ ሲሆን፤ ቋንቋ መተርጎም፣ መረዳት፣ መረጃ መተንተን፣ ጥቆማዎችን መስጠት እና ሌሎችንም ያካትታል።

ይህ ቴክኖሎጂ የህብረተሰብን ገጽታ፣ የግል ሕይወትን ፣ የንግድ እንቅስቃሴን፣ የፀጥታ ሁኔታን፣ የትምህርት፣ የህክምና እና የመረጃ ስርጭት ላይ ፈጣን እና አስፈላጊ እገዛዎችን በማድረግ የመጪውን አለም ቅርጽ ወደ መወሰን እየተሸጋገረ እንደሚገኝ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በዛው ልክ ደግሞ በ100 ሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎችን ስራ ሊነጥቅ እንደሚችል መተንበዩ በአሉታዊ መንገድ የፈጠረው ተጽእኖ ሆኖ ይጠቀሳል።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ.ኤም.ኤፍ) በቅርቡ ባወጣው መረጃ 40 በመቶ የሚሆነው የዓለም ህዝብ በመጪዎቹ አመታት በዚህ ቴክኖሎጂ ስራውን ሊያጣ ይችላል ሲል ትንበያ አስቀምጧል።

አለምአቀፉ የኢንቨስትመንት ባንክ ጎልድማን ሳችስ በ2023 ባወጣው ሪፖርት፤ ሰው ሰራሽ አስተውሎት 300 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎችን የሙሉ ጊዜ ስራ ሊተካ እንደሚችል ይፋ አድርጎ እንደነበር ይታወሳል።

በዚህ ሪፖርት ላይ በአሜሪካ እና አውሮፓ በሰው ልጆች እየተከወኑ ከሚገኙ ስራዎች ውስጥ ሁለት ሶስተኛው በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ሊተካ እንደሚችል ተመላክቷል።

የባንኩ ጥናት፤ የሰው ሰራሽ አስተውሎት መስፋፋት በአለምአቀፍ ደረጃ አመታዊ የሸቀጦች ምርት እና አገልግሎትን በ7 በመቶ እንደሚያሳድግ ይጠበቃል ይላል።

የሰው ሰራሽ አስተውሎት ከሚቆጣጠራቸው የስራ ዘርፎች መካከል 46 ከመቶው አስተዳደራዊ፣ 44 ከመቶው ደግሞ የህግ ዘርፍ ይሆናል ነው የተባለው።

ቢቢሲ ይዞት በወጣው ዘገባ በለንደን ብቻ በሚሊየን የሚቆጠሩ ስራዎች በኤ አይ ሊተኩ እንደሚችሉ አስነብቧል።

እነዚህ የስራ ዘርፎች የሂሳብ ባለሙያዎች ፣ ገንዘብ ተቀባዮች፣ ስልክ በመደወል ምርት እና አገልግሎት የሚሸጡ ባለሙያዎች (ቴሌ ማርኬተርስ) ፣ የፋብሪካ እና የጥገና ሰራተኞች እንዲሁም ዳታ ኢንተሪ ስፔሻሊስት ተቀምጠዋል።

ሴቶች በሰው ሰራሽ አስተውሎት በሚተኩ የስራ ዘርፎች ላይ በብዛት የተሰማሩ መሆናቸውን ተከትሎ የተጽእኖው ቀዳሚ ተጎጂዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ተመላክቷል፡፡

በለንደን ከሰው ሰራሽ አስተውሎት አጠቃቀም እድገት ጋር በተያያዘ አዳዲስ የስራ ቅጥር ማስታወቂያዎች በ38 በመቶ ቀንሰዋልም ነው የተባለው።

በዳዊት በሪሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review