የአውሮፓ ቻምፒንስ ሊግ የሊግ ፎርማት 2ኛ መርሃ ግብር ዛሬ ይጀምራል፡፡ በዕለቱ ከሚከናወኑ ጨዋታዎች ውስጥ ጆዜ ሞሪንሆ ወደ ቀደሞ ቤታቸው ስታምፎርድ ብሪጅ የሚመልሰው የቼልሲ እና ቤኔፊካ ፍልሚያ ይጠበቃል፡፡
በዋና አሰልጣኝነት ስራ የጀመሩበትን ቤኔፊካ የተረከቡት ጆዜ ሞሪንሆ ክለቡን እየመሩ የመጀመሪያ የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡
የ62 ዓመቱ አሰልጣኝ በቼልሲ ደጋፊዎች ያላቸው ቦታ በመጠኑ ቢሸረሸርም አሁንም በበርካቶች ይወደዳሉ፡፡ በአሰልጣኝነት ታሪካቸው የከፍታውን ዘመን በተመለከቱበት ሜዳ ዛሬ የሚኖራቸው አቀባበል ማየት ያጓጓል፡፡
በለንደኑ ክለብ ሦስት የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ያሸነፉት ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ በተለያየ አጋጣሚ ሦስት ክለቦችን እየመሩ ቼልሲን 14 ጊዜ ገጥመዋል፡፡ ጆዜ ከ14ቱ ጨዋታዎች ድል የቀናቸው በአራቱ ብቻ ነው፡፡
በሁሉም ውድድሮች ሦስት ተከታታይ ጨዋታ የተሸነፈው የምዕራብ ለንደኑ ክለብ የዛሬው ጨዋታ ድል በእጅጉ ያስፈልገዋል፡፡ ጣልያናዊው አሰልጣኝ ኢንዞ ማሬስካ ከጫና የሚያላቅቃቸው ድል ማምጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ሁለቱም ቡድኖች የመጀመሪያ የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታቸውን ተሸንፈዋል፡፡ ቼልሲ በባየርን ሙኒክ ፤ ቤኔፊካ በካራባግ መረታታቸው ይታወሳል፡፡
በጨዋታው ቼልሲ ኮል ፓልመር ፣ ሊቫይ ኮልዊል እና ቶሲን አዳራቢዮን በጉዳት ምክንያት አያሰልፍም፡፡ ጨዋታው ምሽት 4 ሰዓት ላይ ይጀምራል፡፡
በሸዋንግዛው ግርማ