የተርክዬ ስታዲየሞች ድባብ እጅግ አስደናቂ ነው፡፡ ደጋፊዎች ቡድናቸውን የሚያበረቱበት መንገድ ይለያል፡፡ የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች ምቾት ተሰምቷቸው እንዳይጫወቱ የሚያደርጉበት መንገድ ያርዳል፡፡
ሊቨርፑል ዛሬ ምሽት በአውሮፓ ካሉ ስታዲሞች ደጋፊዎች በሚያሰሙት ድምፅ ከቀዳሚዎቹ ተርታ በሚመደበው የጋላታሳራይ አሊ ሳሚ የን ስታዲየም ይጫወታል፡፡
አሁን በስፖንሰር ምክንያት ራምስ ፓርክ እየተሰኘ የሚጠራው ስታዲየሙ የጋላታሳራይ ትልቁ ኩራት ነው፡፡ ተጋጣሚያቸውን ’’እንኳን ወደ ገሃነም መጣችሁ’’ ብለው የሚቀበሉት ደጋፊዎች ዛሬ ለቡድናቸው በእጅጉ ያስፈልጋሉ፡፡
ደጋፊዎች ልዩ ድባብ ቢፈጥሩም ጋላታሳራይ ግን ከ2018 በኋላ በአውሮፓ ውድድሮች ካደረጋቸው ስምንት ጨዋታዎች አንድም አላሸነፈም፡፡ በቱርኪዬ አሰልጣኝ ኦካን ቡርክ የሚመራው ጋላታሳራይ የዘንድሮ ውድድርኑም በጥሩ መንገድ አልጀመረም፡፡ በፍራንክፈርት 5ለ1 የተሸነፈው ጋላታሳራይ የመጀመሪያ ነጥቡን ለማግኘት ያጫወታል፡፡

ሊቨርፑል በውድድር ዓመቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሸነፈበት ማግስት የሚያደርገው ጨዋታ ተጠባቂ ነው፡፡ ቀዮቹ አስደናቂ ጅማሮአቸው በክሪስታል ፓላስ የ2ለ1 ሽንፈት ተገትቷል፡፡
የቻምፒየንስ ሊግ ውድድሩን አትሌቲኮ ማድሪድን በማሸነፍ የጀመረው ሊቨርፑል ዛሬ ትልቅ ፈተና ይጠብቀዋል፡፡ አርነ ስሎት በፓላሱ ጨዋታ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ እንዳልተጫወቱ አምነዋል፡፡ ተመሳሳዩን በፈታኙ የጋላታሳራይ ስታዲየም መድገም አይፈልጉም፡፡
ሊቨርፑል ወደ ጋላታሳራይ አቅንቶ ያደረጋቸውን ሁለቱንም ጨዋታዎች አላሸነፈም፡፡ አንዱን አቻ ተለያይቶ በአንዱ ተሸንፏል፡፡ ምሽት 4 ሰዓት በሚከናወነው ጨዋታ ሊቨርፑል በክርስታል ፓላሱ ጨዋታ በቅጣት ያልተሳተፈው ሁጉ ኢኪቲኬን መልሶ ያገኛል፡፡
በጋላታሳራይ በኩል ክብረወሰን ፈራሚያቸው ቪክቶር ኦሲምኸን ወደ ልምምድ ቢመለስም በጨዋታው ስለመሳተፉ አሰልጣኙ ማረጋገጫ አልሰጠም፡፡ በሌሎች የዛሬ ጨዋታዎች ምሽት 1፡45 ሪያል ማድሪድ ከሜዳው ውጪ የካዛኪስታኑን ኪራት አልማቲን ይገጥማል፡፡ በተመሳሳይ ሰዓት አታላንታ ከክለብ ብሩጅ ይጫወታሉ፡፡
ምሽት 4 ሰዓት አትሌቲኮ ማድሪድ ከ ፍራንክፈርት ፣ ቦዶ ከ ቶተንሃም ሆትስፐርስ ፣ ኢንተር ሚላን ከ ስላቪያ ፕራግ ፣ ማርሴይ ከ አያክስ እንዲሁም ፓፎስ ከ ባየርን ሙኒክ ይጫወታሉ፡፡
በሸዋንግዛው ግርማ