ከሃገር ዉስጥና ከዉጭ ሃገር በርካታ ታዳሚዎች የሚሳተፉበት የኢሬቻ በዓል የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ከማቀራረብና ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ከመገንባት ረገድ ትልቅ አስተዋጾኦ እንዳለዉ ተገለጸ፡፡
የኦሮሚያ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ የሚያሰናዳው 45ኛው የጉሚ በለል የውይይት መድረክ ኢሬቻ ለሀገር ማንሰራራት በሚል መሪ ቃል የተካሄደ ሲሆን የኢሬቻን ባህላዊ እሴቶች የተመለከተ የመወያያ ጽሁፍ በምሁራን ቀርቦ ሙያዊ ተካሂዶበታል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ኢሬቻ የኦሮሞ ህዝብ ፈጣሪውን የሚያመሰግንበት ቀን መሆኑን አንስተዋል፡፡ የዘንድሮዉ የሆረ ፊንፊኔና የሆረ ሃርሰዲ የኢሬቻ በአል ባህላዊ እሴቱን በጠበቀ መንገድ እንደሚከበርም አንስተዋል፡፡

በኢሬቻ እሴቶች ላይ ያተኮረዉን የውይይት ጽሁፍ ያቀረቡት በአርሲ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ መሃመድ ነሞ (ዶ/ር) ኢሬቻ የኦሮሞ የምስጋና በአል ስለመሆኑ አብራርተው ኢሬቻ ባለፈው ዘመን ስለተደረገው ፈጣሪን የሚያመሰግኑበት፣ ስለሚመጣው ጊዜም ያማረ ነገር እንዲሆን ጸሎት የሚያቀርቡበት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ኢሬቻ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን በማቀራረብ ፤ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በመስበክ ሀገሪቱን ለተቀረው ዓለም የሚያስተዋዉቅ የኢትዮጵያ አምባሳደር ነው ብለዋል።
ኢሬቻ ድንበር የለውም ያሉት ተመራማሪው የኦሮሞ ህዝብ ዕድሜ፣ ጾታ፣እምነት፣ አካባቢ ሳይገድበው በአንድ ነት ተሰባስቦ ባህሉን የሚያንጸባርቅበት፤ ወንድማማችነቱን የሚያጠናክርበት ነዉ ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በ-ምትኩ ተሾመ