የኢሬቻ በዓል እሴቱን ጠብቆ በደመቀ ሁኔታ እንዲከበር አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉን በብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽ/ ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ ገልጸዋል።
የኢሬቻ በዓል ባህላዊ ትውፊቱን ጠብቆ አንድነትን በሚያጎላ መልኩ ለማክበር አዲስ አበባ ከተማ ቅድመ ዝግጅቷን ቀጥላለች፡፡ በየካ ክፍለ ከተማም የኢሬቻ ፌስቲቫልን በማስመልከት የውይይት መድረክ ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ ላይ የተገኙት በብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽ/ ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ፤ የፍቅር እና የአንድነት ተምሳሌት የሆነው የኢሬቻ በዓል በደመቀ ሁኔታ እንዲከበር አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡

በዓሉን ለማክበር ወደ ከተማዋ የሚመጡ እንግዶችን በኢትዮጵያዊ እንግዳ ተቀባይነት ባህል በማስተናገድ ባህላዊ ትውፊቱን ጠብቆ አብሮነትን በሚያጎላ መልኩ እንዲከበር ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
የየካ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ፍፁም ሀይሌ በበኩላቸው፤ የኢሬቻ በዓል የፍቅር እና የአንድነት ምልክት መሆኑን ገልፀዉ፤ ይህን የጋራ እሴት የሆነውን በዓል ለትዉልድ እንዲተላላፍ በትብብር መስራት ይጠብቅብናል ብለዋል፡፡
የዘንድሮ ኢሬቻ በዓል መስከረም 24 በአዲስ አበባ እንዲሁም መስከረም 25 ቀን 2018 ዓ.ም በቢሾፍቱ ይከበራል።
በ-ቴዎድሮስ ይሳ