አምራችና ብቁ ዜጋ ለመፍጠር በትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚፈጸሙ አዋኪ ድርጊቶችን ማስቀረት እንደሚገባ ተገለፀ

You are currently viewing አምራችና ብቁ ዜጋ ለመፍጠር በትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚፈጸሙ አዋኪ ድርጊቶችን ማስቀረት እንደሚገባ ተገለፀ

AMN-መስከረም 20/2018 ዓ.ም

አምራችና ብቁ ዜጋ ለመፍጠር በትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚፈጸሙ አዋኪ ድርጊቶችን ማስቀረት እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን አዋኪ ድርጊቶችን እና በስነ ምግባር ብልሹ አሰራርን ለማስቀረት ያለመ ውይይት ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት እያካሄደ ይገኛል።

በውይይቱ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ፤ በመዲናዋ በተለያዩ ዘርፎች የሚስተዋሉ ህገ-ወጥ ተግባራትን ለመከላከል በተሰራው ስራ የደንብ መተላለፍ ጥሰትን መቀነስ መቻሉን ገልፀዋል።

በትምህርት ቤቶች አካባቢ ጫት፣ ሽሻ፣ መጠጥ፣ ቁማር ቤቶች እንዲሁም ፔንሲዮኖች የሚከፍቱ አካላት አሉ ያሉት ሻለቃ ዙሪሁን፤ ይህን ተግባር ሆን ብለው የሚፈጽሙ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ በአጽንኦት አሳስበዋል።

ዋና ስራ አስኪያጁ አክለውም፤ በመዲናዋ በትምህርት ቤቶች ዙሪያ አዋኪ ተግባራት በሚፈጽሙ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ሁሉም ጥቆማ በመስጠት የበኩሉን መወጣት እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል፡፡

መሰል ተግባራትን ሲያስተውል ለሚመለከተው በመጠቆም ሚናቸውን እንደሚወጡ ኤ ኤም ኤን ያነጋገራቸው የውይይቱ ተሳታፊዎች ተናግረዋል።

ተሳታፊዎቹ አዋኪ ተግባራት የማህበረሰቡ ጠንቅ በመሆናቸው በትኩረት መከላከል እንደሚገባ ገልፀዋል።

በመድረኩ አዋኪ ድርጊቶችን መከላከልና ብልሹ አሰራር እንዲሁም ሌብነት ለመከላከል የህብረተሰብ ሚና የሚሉ ሁለት የመነሻ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በመሀመድኑር ዓሊ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review