የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የጋዛን ጦርነት ለማስቆም ያቀረቡት የሰላም ስምምነት ሀሳብ በእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ተቀባይነት አግኝቷል።
ኔታንያሁ ትራምፕ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት ከተመለሱ ጀምሮ አራተኛ ጉብኝታቸውን በትላንትናው ዕለት አድርገዋል።
ትራምፕ ያቀረቡት እና እስራኤል የተቀበለችው የሰላም ስምምነት ደም አፋሳሹን ጦርነት ለማስቆም ይኖረዋል ተብሎ በሚጠበቀው ሚና፤ በመካከለኛው ምስራቅ አረብ ሀገራት እና በአውሮፓውያን ከፍተኛ ድጋፍ ተችሮታል።
ስምምነቱ በውስጡ የያዛቸው ዋና ዋና ነጥቦች ምንድን ናቸው?
ዶናልድ ትራምፕ ያቀረቡት የሰላም ሀሳብ ጦርነቱ በአስቸኳይ እንዲቆም እና የሀማስ ታጣቂ ቡድን 20 በህይወት የሚገኙ ታጋቾችን እንዲለቅ ይጠይቃል።
በተጨማሪም 24 የሚጠጉ ህይወታቸው ያለፉ ታጋቾች አስክሬን እንዲመለስ፤ በምላሹ በ100ዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን እስረኞችን እስራኤል እንድትለቅ የሚጠይቅ ነው።
ከጦርነቱ በኋላ በሚኖረው የጋዛ አስተዳደር ውስጥ ሀማስ ቦታ እንዲኖረው የሚጠይቀው የሰላም ድርድር ሀሳብ፤ ቡድኑ ለእስራኤል የደህንነት ስጋት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲሰጥ አዟል።
ይህ የማይሆን ከሆነ እና ሀማስ ይህን የሰላም ስምምነት የማይቀበል ከሆነ እስራኤል በቡድኑ ላይ የጀመረችውን ዘመቻ አጠናክራ እንድትቀጥል አሜሪካ ሙሉ ድጋፍ አደርጋለሁ ብላለች።
ሁለቱ መሪዎች የሰጡትን የጋራ መግለጫ ተከትሎ ሞሀሙድ አባስ የሚመሩት የፍልስጤም አስተዳደር፤ የሰላም ስምምነቱን እንደሚቀበለው እና በአካባቢው ሰላም ለማስፈን ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ገልጿል።
ከዚህ ባለፈ ሳኡዲ አረብያ ፣ ቱርክ ፣ ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ፣ ኳታር ፣ ኢንዶኔዢያ ፣ ፓኪስታን ፣ ዮርዳኖስ እና ግብጽ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸው በኩል ባወጡት የጋራ መግለጫ ስምምነቱን አወድሰዋል።
ብሪታንያ፣ ፈረንሳይ እና የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ ሌሎች የምዕራባውያን ሀገራት እና የባለብዙ ወገን ድርጅቶች ለስምምነቱ መፈጸም ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
በዳዊት በሪሁን