የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተገልጋዩ በነፃነት አገልግሎት የሚያገኝበት ቦታ መሆኑ ተገለፀ

You are currently viewing የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተገልጋዩ በነፃነት አገልግሎት የሚያገኝበት ቦታ መሆኑ ተገለፀ

AMN – መስከረም 20/2018 ዓ.ም

የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ ተገልጋዩ በህገ-ወጥ መንገድ ገንዘብ እጠየቃለሁ ብሎ ሳይሰጋ በነፃነት አገልግሎት የሚያገኝበት ቦታ ነው ሲሉ የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ አለማየሁ ከኤ ኤም ኤን 24/7 ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል፡፡

የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት (አዲስ የአገልግሎት አድማስ) በሚል በከተማ ደረጃ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

ማዕከሉ በአደረጃጀትም፣ በአሰራር ስርዓት እንዲሁም በሥነ-ምግባር አርአያ የሆኑ ሰራተኞች እና ጠንካራ የአሰራር ስርዓት ተይዞ ወደ ስራ መገባቱን ነው የገለጹት፡፡

ማዕከሉ በከተማ አስተዳደር ደረጃ ባሉ 13 ተቋማት ተቀናጅተው የዲጂታል አገልግሎት እንደሚሰጡበትም አመላክተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ሁለት ባንኮች እና አራት የሚሆኑ የፌዴራል ተቋማትን ማካተቱንም አቶ ዮናስ ገልጸዋል፡፡

እነዚህ 13 ተቋማትም በድምሩ 107 የሚሆኑ አገልግሎቶችን ለመስጠት በሚያስችል ሁኔታ ለዚሁ ተግባር በሀገር አቀፍ ደረጃ የለማውን የመሶብ ሥርዓት በመጠቀም ወደ ሥራ መግባታቸውን ነው የገለጹት፡፡

የመሶብ አገልግሎት መጀመር የተገልጋይን እንግልት ለመቀነስ፣ የሚያባክነውን ጊዜ ለመቆጠብ እና ህብረተሰቡ ከዚህ ቀደም ቅሬታ ያነሳባቸው የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በተቋሙ ስር ያሉት አሥራ ሦስት ተቋማት የሲቪል ምዝገባ እና ኢኮኖሚ ዘርፍን ጨምሮ በሶስት ዘርፎች መደራጀታቸውን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በወረዳና በክፍለ ከተማ የሚሰጡ አገልግሎቶች እንደተጠበቁ ሆነው ከአንድ በላይ አገልግሎቶችን ማግኘት ለሚፈልግ ተገልጋይ ቀልጣፋ አገልግሎቶችን ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ማዕከሉ አገልግሎት አሰጣጥን ቀልጣፋ ከማድረግ ባለፈም፤ ከህገ-ወጥ ደላላ የጸዳ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በዚህም ተገልጋዩ ያለ አግባብ በህገ-ወጥ መንገድ ገንዘብ እጠየቃለሁ በሚል ሳይሰጋ በነፃነት አገልግሎት የሚያገኝበት ቦታ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

ሰራተኞችም መልካም ሥነ-ምግባር ያላቸውና ጠበቅ ያለ የሥነ-ምግባር መመሪያ እንዲከተሉ የሚገደዱበት ሆኖ መደራጀቱንም ነው ያብራሩት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተገኙበት የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በአዲስ አበባ ደረጃ ጳጉሜን 5 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ ወደ አገልግሎት መግባቱ ይታወሳል፡፡

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review