የኢሬቻ በዓልን ለማክበር ለሚመጣው እንግዳ በፍፁም ትሕትና የተሞላበት አቀባበል ለማድረግ በቂ የቅድመዝግጅት ስራ መከናወኑ ተገለፀ።

You are currently viewing የኢሬቻ በዓልን ለማክበር ለሚመጣው እንግዳ በፍፁም ትሕትና የተሞላበት አቀባበል ለማድረግ በቂ የቅድመዝግጅት ስራ መከናወኑ ተገለፀ።

AMN – መስከረም 20/2018 ዓ.ም

እኔም ለአካባቢዬ ሰላም ዘብ ነኝ በሚል መሪ ሃሳብ የዘንድሮውን የኢሬቻ በዓል በሰላምና በድምቀት ለማክበር የሚያስችል የጋራ ጥምር የፀጥታ ኃይል በአንድ ማዕከል ስምሪት ተሰጥቷል ።

የኢሬቻ በዓል በርካታ ታዳሚዎች እና ጎብኝዎች ከሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ የሚሳተፉበት መሆኑን ተከትሎ፤ እንግዶችን በፍፁም ትሕትና የተሞላበት አቀባበል ለማድረግ በቂ የቅድመዝግጅት ስራ መከናወኑ ተገልጿል።

የአዲስ አበባ ከተማና የሸገር ከተማ የጋራ ጥምር የፀጥታ ኃይል በለሚኩራ ክፍለከተማ በአንድ ማዕከል ስምሪት የመስጠት መርሐግብር ተከናውኗል።

የጋራ ጥምር የፀጥታ ኃይል ውስጥ ከፌደራል ፖሊስ፣ ከአዲስአበባ ፖሊስ፣ እንዲሁም ከለሚኩራ ክፍለከተማ ደንብ ማስከበር አባላት የሰላም ሰራዊት አባላት እና ከሸገር ከተማ ክፍለከተሞች ፤ ኤካ ጣፎ፣ ኩራ ጅዳ እና ኮዬ ፈጬ የተውጣጡ የፀጥታ አካላት ተሳታፊ መሆናቸው በመድረኩ ተገልጿል።

በመርሀ-ግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ አዲስ አበባ የለውጥ ግስጋሴ ውስጥ እንደምትገኝ ገልፀው፤ ይህን የሚመጥን በቴክኖሎጂ የተደገፈ የፀጥታና የደሕንነት የማረጋገጥ ተግባራት በማከናወን ሰላሟ የተጠበቀ ከተማን መፍጠር ተችሏል ብለዋል።

ይህንንም በከተማዋ በሚሊየን የሚቆጠር ሕዝብ የሚሳተፍባቸው የአደባባይ በዓላትን በሰላም ማሳለፍ መቻላችን አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል ኃላፊዋ።

አክለውም ከፊታችን የሚከበረውን የኢሬቻ በዓል ለመሳተፍ የሚመጣው እንግዳ በሰላም መጥቶ በሰላም እንዲመለስ ፍፁም ትሕትና የተሞላበት አቀባበል እና ያለምንም ተግዳሮት በዓሉ እንዲከበር የሚያስችል በቂ የቅድመዝግጅት ስራ መከናወኑን ገልፀዋል።

የከተማችንን ሰላም ለማወክ የፅንፈኛና የፀረ ሰላም ሃይሎች በርካታ እቅዶችን ማክሸፍ የቻልነው በቅንጅት ተልዕኮችን መወጣት በመቻላችን ነው ያሉት ቢሮ ኃላፊዋ፤ አሁንም ከፌደራል እንዲሁም ከሸገር ከተማ የፀጥታ መዋቅር ጋር የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ በመሆን ፍፁም ሰላማዊ የሆነ በዓል ማሳለፍ ይገባናል ሲሉም አሳስበዋል።

የለሚኩራ ክ/ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አድማሱ ደቻሳ በበኩላቸው፤ ኢሬቻ ከገዳ ስርዓት የተገኘ በአደባባይ የሚከበር ታላቅ በዓል መሆኑን አንስተው ፤ በዓሉ ላይ ለመሳተፍ የሚመጡ እንግዶችን በገዳ ስርዓት ለመቀበልና ለመሸኘት ለሚኩራ ክ/ከተማ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን ገልጸዋል።

የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል መስከረም 24 በሆረ ፊንፊኔ እንዲሁም መስከረም 25 ደግሞ በቢሾፍቱ ሆረ ሀርሰዲ እንደሚከበር ይታወቃል፡፡

በታምሩ ደምሴ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review