በዘመነ ዲጂታል የማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገጾች አይነት እና ብዛት መጨመር ሰዎች ከኢንተርኔት ጋር በተያያዘ የሚያጠፉት ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር አድርጓል።
የማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገጾች በሺህ ኪሎሜትር ርቀት ላይ በተለያየ ስፍራ እና ማንነት የሚገኘውን የአለም ህዝብ በማቀራረብ የተለያዩ ሀሳቦች እና መረጃዎች እንዲዘዋወሩ በር ከፍተዋል።
ከዚህ ባለፈም በንግድ ፣ በመዝናኛ ፣ በመረጃ እና በሌሎችም ዘርፎች ሰዎች ቀድመው እንዲገኙ እንዲሁም ትስስራቸውን እንዲያጠናከሩ አስችለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሀሰተኛ እና አሳሳች መረጃዎች መጠን እንዲጨምርና ማህበራዊ መስተጋብር እንዲሳሳ ከማድረጉ አንጻር የማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገጾች ያላቸዉ ሚናቸው ቀላል የሚባል አይደለም።
ስታቲስታ ይዞት የወጣው መረጃ እንደሚያመላክተዉ አንድ ሰው በአማካኝ በቀን 2 ሰዓት ከ24 ደቂቃ ሶሻል ሚዲያ ላይ እንደሚያባክን አስቀምጧል።
በአሁኑ ወቅት 58.4 በመቶ የሚሆነው የአለም ህዝብ የማህበራዊ ሚዲያዎች ተጠቃሚ ሲሆን በ2025 ይህ ተጠቃሚ በአጠቃላይ 4 ትሪሊየን ሰዓት በማህበራዊ ገጾች ላይ ያጠፋል ተብሏል።
ሰዎች ከማህበራዊ ሚዲያዎች ማግኘት እንደሚፈልጉት ይዘት እና መረጃ ሰፊ ጊዜ የሚያጠፉባቸው ገጾች ቢለያዩም ፌስቡክ ፣ ዩትዩብ ፣ ቲክቶክ እና ኤክስ በበርካታ ተጠቃሚዎች የሚጎበኙ ገጾች መሆናቸው ተመላክቷል።
በአለም ላይ በርካታ ጊዜያቸውን በማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገጾች ላይ የሚያጠፉ ዜጎችን ይፋ ያደረገው የስታቲስታ ሪፖርት ፊሊፒንስን ቀዳሚ አድርጓታል።
የፍሊፒንስ ዜጎች በአማካኝ በቀን ለ4 ሰዓት ከ6 ደቂቃ ማህበራዊ ገጾች ላይ የሚያሳልፉ ሲሆን ፤ ኮሎምቢያ በ3 ሰዓት ከ46 ደቂቃ ትከተላለች።
ደቡብ አፍሪካ ፣ ብራዚል ፣ አርጄንቲና፣ ሳኡዲአረቢያ እና ሜክሲኮ 3 ሰዓት እና ከዛ በላይ ጊዜን ሶሻል ሚዲያ ላይ የሚያጠፉ ዜጎች የሚገኙባቸው ሀገራት ሆነው በደረጃ ተቀምጠዋል።
እርስዎስ በቀን ዉስጥ ምን ያህል ሰዓታትን የማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገጾችን በመጠቀም ያሳልፉ ይሆን?
በዳዊት በሪሁን