የሆረ ፊንፊኔ እና ሆረ ሀርሰዴ የኢሬቻ በዓል አከባበር

You are currently viewing የሆረ ፊንፊኔ እና ሆረ ሀርሰዴ የኢሬቻ በዓል አከባበር

AMN- መስከረም 21/2018 ዓ.ም

በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠዉ የኢሬቻ በዓል፣ በሆረ ፊንፊኔ እና በሆረ ሀርሰዴ በየዓመቱ ከመስከረም ወር አጋማሽ በኋላ በድምቀት ይከበራል፡፡

ኢሬቻ የኦሮሞ ህዝብ ከባዱን የክረምት ወቅት አልፎ ለብርሃን ስለበቃ፣ በክረምቱ በወንዝ ሙላት የተነሳ መገናኘት ያልቻሉ ሰዎች መገናኘት በመቻላቸው ለፈጣሪው (ለዋቃ) ምስጋና የሚያቀርብበት ትልቅ በዓል ነው ሲሉ በኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን የባላህዊ ቅርሶች ከፍተኛ ተመራማሪና አስተባባሪ አቶ ተስፋፂዮን ዮሴፍ ይገልፃሉ፡፡

ከማህበራዊ መስተጋብር አኳያም ሰዎች የሚሰባሰቡበትና የሚገናኙበት ሲሆን፣ በአንፃራዊ ከባዱ የክረምት ወቅት አልፎ ብርሃን (ብራ) ስለደረሰ ለዛ ምልክት ይሆን ዘንድ የለመለመ ሣር ይዘው ወደ ወንዝ በመውረድ ንጹህ ውሃ እየነከሩና እየረጩ ለፈጣሪ ምስጋና የሚያቀርቡበት እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ይህንንም የምስጋና ሥርዓት ሆረ ፊንፊኔ እና ሆረ ሀርሰዴን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች በተከታታይ ቀናት እንደሚያከብረው ገልጸዋል፡፡

ከመላው ኢትዮጵያና ከዉጭ ሃገራት ጭምር የመጡ የበዓሉ ታዳሚዎች ከዋዜማ ጀምሮ በአሉ በሚከበርበት ስፍራ በሆረ ፊንፊኔ በመሰባሰብ ፤ የተለያዩ ባህላዊ ጭፈራዎችን በማዜምና ምስጋና በማቅረብ አድረው በነጋታው ዋናውን የምስጋና በአል እንደሚያከብሩም ገልጸዋል፡፡

በዚህ በአል ላይ በዋናነት ታዳሚዎች የደስታና የምስጋና ምልክት የሆነውን ባህላዊ ነጫጭ ልብስ ለብሰው፣ ባህልን የሚያንፀባርቁ የተለያዩ ሁነቶችን በመከወን በተለይም ዜማዎችን በማዜም ፣ ግጥሞችን በማቅረብ፣ ወደ ፈጣሪ በመጸለይ እና ምስጋና በማቅረብ ሥርዓቱ ይከናወናል ብለዋል፡፡

በዓሉ ፍቅር፣ አንድነት፣ መተሳሰብ የሚገለፅበት በመሆኑ እያንዳንዱን ሁነት በጋራ እንደሚያከናውኑ በማንሳትም፣ ይህም የአንድነትና የፍቅር መገለጫ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የኦሮሞ አባቶች ከብዙ ዓመታት በፊት ጀምሮ በሆረ ፊንፊኔ እና በሆረ ሀርሰዴ የኢሬቻ ማክበሪያ ቦታ በመገናኘት ይህንን በዓል ሲያከናውኑ እንደቆዩ ታሪክ እንደሚያስረዳ ገልጸዋል፡፡

ይህ በዓል የገዳ ሥርዓት አንዱ አካል እንደመሆኑ፣ በትውልድ ቅብብሎሽ ዛሬ ላይ ደርሶ አሁን ባለው ትውልድም እየተከበረ እንደሚገኝ ነው በኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን የባላህዊ ቅርሶች ከፍተኛ ተመራማሪና አስተባባሪ አቶ ተስፋፂዮን ዮሴፍ ከኤ ኤም ኤን ዲጂታል ጋር ነበራቸው ቆይታ ያስረዱት፡፡

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review