የስኳር በሽታ ታካሚዎች ከህመሙ አንጻር በአመጋገብ ዙሪያ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸዉ ባለሙያዎች ይመክራሉ።
በተለይ የስኳር መጠናቸው ከፍና ዝቅ እንዳይል የታሸጉ ምግቦች አለመጠቀም እንዲሁም በተለያዩ ምግቦችና መጠጦች ውስጥ ስኳር ከመጨመር ይልቅ ተፈጥሯዊ ማጣፈጫ ምግቦች በመተካት የአመጋጋብ ስርአትን ማስተካከል እንደሚቻል ነዉ የስነ ምግብ ባለሙያዋ ኬብሮን ሰናይ የሚመክሩት።
የስኳር ህመም እና ሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ ህመሞች በሚኖሩበት ጊዜ ብዙ የሚከለከሉ የምግቦች ዓይነቶች እንዳሉ ይገልጻሉ። በዋናነት የስኳር ህመም በሚኖርበት ጊዜ ሙሉ ለሙሉ ወይንም በፍፁም እንዳይጠቀሙ የሚመከረው የምግብ ዓይነትና ግብአት ነጭ ስኳር እና በዚሁ ስኳር የተዘጋጁ በፋብሪካ ያለፉ የታሸጉ ምግቦች እና መጠጦች ናቸዉ።

እንዲሁም ለቡናና ሻይ የምንጠቀመውን ስኳር ጨምሮ የለስላሳ መጠጦች ማጣፈጫ ያለባቸውን ምግቦች በፍፁም መጠቀም እንደማይመከር ነው ባለሞያዋ ኬብሮን ሰናይ ከኤኤምኤን ጋር በነበራቸዉ ቆይታ ያብራሩት።
ምግቦቹ ለመከልከላቸው ያስቀመጡት ምክንያትም በቀላሉ ሰውነት ውስጥ በመግባት የደም ስኳር መጠንን ከፍ በማድረግ ሰውነታችን በሚፈለገው መጠን ላይ ተረጋግቶ እንዳይቆይ በማድረግ ሌሎች የጤና እከሎችን ያስከትላል የሚል ነዉ። የስኳር በሽታ ታካሚዎች በተፈጥሮ የሚገኙ ምግቦችን በትክክለኛ መንገድ በማብሰል መጠቀም እንደሚችሉም መክረዋል፡፡
ሆኖም ግን አሁን ላይ የታሸጉ ምግቦችን መጠቀም እየተለወጠ ካለው የአኗኗር ዘይቤ ጋር ብዙዎች ጋር እየተለመደ መምጣቱን ያነሱት ባለሞያዋ የምንጠቀመው ማንኛውም ምግብ ላይ ስኳር መጨመር እና አለመጨመሩን መለየት ባህል ሊሆን ይገባል ብለዋል። ፡፡

ነገር ግን በተፈጥሮ ለምግብ የምንጠቀምባቸው ዝንጅብል፣ነጭ ሽንኩር እንዲሁም ቀረፋና ሌሎች ተፈጥሯዊ ማጣፈጫዎች ተጨማሪ የጤና ጥቅም ስላላቸው መጠቀም እንደሚገባ ነው ምክራቸውን የለገሱት ፡፡
አንድ የስኳር ታማሚ እንደ ድንች ያሉ የተከለከሉ ምግቦችን መመገብ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘና ታማሚው ቀድሞ የሚመገባቸው ከሆነ ከመመገቡ ከአንድ ቀን በፊት በመቀቀል አሊያም በማብሰል ፍሪጅ ውስጥ በማስቀመጥ በሚፈለገው ጊዜ በማሞቅ መጠቀም እንደሚቻል ነው የስነ-ምግብ ባለሞያዋ ኬብሮን ሰናይ የገለፁት ፡፡
በያለው ጌታነህ