የትራፊክ ምልክት ነቅለው የወሰዱ ተከሳሾች በቁጥጥር ስር ውለው በ6 ዓመት ፅኑ እስራት መቀጣታቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ገለፀ

You are currently viewing የትራፊክ ምልክት ነቅለው የወሰዱ ተከሳሾች በቁጥጥር ስር ውለው በ6 ዓመት ፅኑ እስራት መቀጣታቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ገለፀ

AMN – መስከረም 21/2018 ዓ.ም

በኮሪደር ልማቱ ላይ የተሰራ የትራፊክ ምልክት ነቅለው የወሰዱ ተከሳሾች በቁጥጥር ስር ውለው በ6 ዓመት ፅኑ እስራት መቀጣታቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታውቋል፡፡

መመሪያው ለኤ ኤም ኤን በላከው መረጃ፤ ተከሳሾቹ በኮሪደር ልማቱ ላይ ከተተከለው የትራፊክ ምልክ ባሻገር በተጨማሪ 6 የቆሻሻ ማጠራቀሚያዎችን መስረቃቸውንም በምሪት አሳይተዋል፡፡

የወንጀል ድርጊቱ የተፈፀመው መስከረም 4 ቀን 2018 ዓ/ም ከሌሊቱ 10፡00 ሠዓት በለሚ ኩራ ክ/ከተማ ወረዳ 8 ልዩ ቦታው ካምብሪጅ ትምህርት ቤት አካባቢ መሆኑን ተገልጿል፡፡

ተከሳሾች ታረቀኝ ታፈሰ እና አፈወርቅ ዮናስ በኮሪደር በለማ መንገድ ላይ ተተክሎ የነበረ የመንገድ ዳር የትራፊክ ምልክት ነቅለው ይዘው ሲሄዱ በወቅቱ በወንጀል መከላከል ስራ ላይ በነበሩ የፖሊስ አባላት እጅ ከፍንጅ ሊያዙ መቻላቸውን ፖሊስ ገልጿል፡፡

ፖሊስም ተከሳሾችን ይዞ ባደረገው ምርመራን የማስፋት ተግባር በኮሪደር በለማ መንገድ ላይ ዳር ተቀምጦ የነበረ የዋጋ ግምታቸው 2 መቶ ሺህ ብር የሚያወጣ 6 የቆሻሻ ማጠራቀሚያዎችን በመስረቅ በአካባቢው ለሚገኙ 3 ተቀባዮች በ8 ሺህ ብር የሸጡ መሆኑን አምነው ቃላቸውን በመስጠታቸው ተቀባዮችን በቁጥጥር ስር በማዋል ኤግዚቢቶቹን ማስመለስ መቻሉን የምርመራ መዝገቡ እንደሚያስረዳ ፖሊስ ገልጿል፡፡

ተከሳሾች ታረቀኝ ታፈሰ እና አፈወርቅ ዮናስ በፈፀሙት የትራፊክ ምልክት የስርቆት ወንጀል የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ለሚ ኩራ ምድብ 3ኛ ወንጀል ችሎት በ6 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ የወሰነባቸው ሲሆን በቀጣይም በፈፀሙት የመንገድ ዳር የቆሻሻ ማጠራቀሚያዎችን ስርቆት ወንጀል ለውሳኔ ጥቅምት 6 ቀን 2018 ዓ/ም እንዲቀርቡ በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መሰጠቱን ፖሊስ በላከው መረጃ አስታውቋል፡፡

በመሰረተ ልማቶች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች በህዝብ ሀብት ላይ የሚፈፀሙ በመሆናቸው ህብረተሰቡ መሠል የወንጀል ድርጊቶችን ሲመለከት ለአቅራቢያው የፀጥታ አካል መረጃ ሊሰጥ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አሳስቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review