በመደመር መንግሥት መጽሃፍ ላይ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው። በውይይቱም ሙሁራን የመጽሀፉ ጭብጥ ላይ ሙያዊ እይታቸውን አጋርተዋል።
በኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዮሴፍ ቤካ (ዶ/ር)፣ መጽሀፉ ሀገረ መንግሥትን በሚመራው መሪ መጻፉ ልዩ እንደሚያደርገው ገልጸው፣ አስተሳሰብን፣ ፍልስፍናን ርዕዮተ ዓለምን ያካተተ ነው ብለዋል።
በተለዋዋጭ ዓለም ውስጥ ኢትዮጵያ ያለችበትንና የደረሰችበትን ደረጃ በመጠየቅ የሀገር አለማደግና ድህነት በጸሀፊው በቁጭት መታየቱንም ተናግረዋል። ባለፉት ዘመናት መሪዎች የነበሩ ድክመቶችንና ጥንካሬዎችንም በመዳሰስ ለምን ወደ ኋላ ቀረን በማለት ጸሀፊው ከጊዜ ጋር መሽቀዳደማቸውንም ዳሰዋል።

እንደ ኢትዮጵያ ማደግ ለሚፈልጉ ሀገራትም አስፈላጊ እሳቤን ያካተተ ስለመሆኑ ነው መምህሩ ያመላከቱት። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህርና ተመራማሪው ዳኛቸው አሰፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ መጽሀፉ የማህበራዊ ፖለቲካ ስብራትን ማሳየቱን ዳሰዋል።
ምክንያታዊነትን አብዝቶ የሚያወድሰው መጽሀፉ፣ ችግር ለመፍታት ከብዙ ወገን መዘጋጀት ያስፈልጋል ብሎ እንደሚያምንም ተናግረዋል።መምህሩ አክለውም፣ ጊዜን መርሁ ያደረገው መጽሀፉ፣ የወደ ፊቱን ይተልማል፤ ያለውንም ይጠብቃል ነው ያሉት፡፡
በመደመር መንግሥት መጽሀፍ ጭብጦች ላይ ባተኮረው የውይይት መርሀ ግብር ሙሁራን፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ነው።
ፍቃዱ መለሰ